በአማራ ክልል በድምቀት ለሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት በቂ የጸጥታ ስምሪት ማከናወኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

103

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በድምቀት ለሚከበሩ የልደት እና የጥምቀት በዓላት በቂ የጸጥታ ስምሪት መደረጉን የክልሉ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለኢቢሲ እንደገለጹት፤ የጥር ወር ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ተግባራት በጋራ የሚከወኑበት መኾኑን በመግለፅ፣ ልደትን በላልይበላ፣ጥምቀትን በጎንደር እና ጥርን በባሕርዳር ክዋኔዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ በቂ የጸጥታ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ሃይማኖታዊ በዓላቱ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ገጽታ ግንባታ ወሳኝ ክዋኔዎች ከመኾናቸው በተጨማሪ ካላቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር ጎብኝዎች ምቹ ጊዜ እንዲያሳልፉ ማኅበረሠቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን በመኾን የተለመደ ትብብር እንዲያደርግም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሠላምን ለመገንባት በተሠራ የማኅበረሠብ አቀፍ ሥራ ከ400 በላይ በቅማንት ማኅበረሠብ ስም በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወጣቶች በተሃድሶ ስልጠና በመመረቅ ወደ ማኅበረሠቡ መቀላቀላቸውንም አመልክተዋል።

ክልሉ ባለፉት ዓመታት በውስጥና የውጭ ኃይሎች የገጠመው የፀጥታ ችግር ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፣ ሀገራዊ የሠላም ስምምነቱን ተከትሎ ህብረተሠቡ ያገኘውን እፎይታ ለማስቀጠል እየተሠራ መሆነን ገልፀዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሠላም ለመገንባት የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ማኅበረሠቡን ያሳተፈ የሠላም ምክር ቤት በመመስረት በተሠራው የሠላም ግንባታ ሥራ ፣በጎንደር እና አካባቢው የኅብረተሠቡ የሠላም ስጋት የኾነውን እገታ፣ግድያ እና ዝርፊያ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችን ለሕግ የማቅረብ እና የማስታገስ ሥራ መሠራቱንም ቢሮው አስታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የቅዱስ ላል ይበላን እና አካባቢውን ዓለም አቀፍ ቅርሶች ለዓለም በድጋሚ የምናስተዋውቅበት ጊዜ አሁን ነው” አስጎብኝዎች
Next articleየኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ያለምንም የፀጥታ ስጋት ለማክበር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናዎናቸውን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡