“የቅዱስ ላል ይበላን እና አካባቢውን ዓለም አቀፍ ቅርሶች ለዓለም በድጋሚ የምናስተዋውቅበት ጊዜ አሁን ነው” አስጎብኝዎች

94

ወልድያ፡ ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አስጎብኝ ማኅበራት ወደ ላል ይበላ የሚመጡ ቱሪስቶች እና እንግዶች ተገቢውን መረጃ አግኝተው እና አካባቢውን ተዋውቀው እንዲመለሱ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በተለይም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ላል ይበላ እና አካባቢው ቱሪስት አስጎብኝ ማኅበር አባል እና አስጎብኝ የኾነው መለሰ አሰፋ እንደነገረን፤ የቅዱስ ላል ይበላ እና አካባቢው ዓለም አቀፍ ቅርሶች ለዓለም ሕዝብ ጎብኝ ቅርብ ከኾኑ የኢትዮጵያ መዳረሻዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት በኮሮና እና ጦርነት ምክንያት የጎብኝዎች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱ ለከተማዋም ኾነ መተዳደሪያቸው በቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረቱት ሁሉ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መቆየታቸውን ነግሮናል፡፡

አሁን በሀገሪቱ ያለው አንጻራዊ ሰላም አካባቢው የሚታወቅበትን የልደት በዓልን በድምቀት ለማክበር እና ጎብኝዎችን ለማሰብ እድል ፈጥሯል የሚለው አስጎብኝው “የቅዱስ ላል ይበላን እና አካባቢውን ዓለም አቀፍ ቅርሶች ለዓለም በድጋሚ የምናስተዋውቅበት ጊዜ አሁን ነው” ብሎናል፡፡

ከቱሪዝም እንቅስቃሴው ከሚገኘው ጊዜያዊ ጥቅም ባለፈ የአካባቢውን ጥንታዊ ታሪክ፣ ሃይማኖት እና ማንነት ለቀሪው ዓለም ማሳወቅ የጉዞ ማኅበራት ድርብ ኅላፊነት ነው ያለን ደግሞ የቅዱስ ላል ይበላ እና አካባቢው ቱሪስት አስጎብኝ ማኅበር ሊቀ መንበር እስታሉ ቀለሙ ነው፡፡ አካባቢው በቅርብ ዓመታት ከተፈጠሩት ችግሮች በፊት የዓለም ሕዝብ የቱሪስት መዳረሻ ነበር የሚለው አቶ እስታሉ የቀደመውን የቱሪስት መዳረሻነት ለመመለስ እና አካባቢውን በሚገባ ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ነግሮናል፡፡

ወደ ቅዱስ ላል ይበላ የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ስለ ገዳሙ እና ዓለም አቀፍ ቅርሱ መረጃ የሚያገኙበት የመረጃ ማዕከል አንድ ብቻ እንደነበር ከቅዱስ ላል ይበላ ገዳም ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር የውጭ ግንኙነት ክፍል ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የሙዚየም እና ትኬት ቢሮ ሥራ አስኪጅ ዲያቆን መኮንን ገብረ መስቀል ጎብኝዎች በተጨማሪ መረጃ የሚያገኙበት የመረጃ ማዕከላት እየተከፈቱ ነው ብሎናል፡፡

የልደትን በዓል በላል ይበላ ለማክበር ወደ ደብረ ሮሃ የሚመጡ እንግዶች የመረጃ ችግር እንዳይገጥማቸው ሕጋዊ አስጎብኝዎች ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ያሉት ዲያቆን መኮንን እንግዶች በቆይታቸው ተደስተው የሚመለሱበት እና ዓለም አቀፍ ቅርሱን ዳግም ለዓለም ሕዝብ የምናስተዋውቅበት መልካም አጋጣሚ በመኾኑ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጣና ዳርቻ የማልማት ፍላጎታችን የሐይቁን ዘላቂ ጤና የማይጎዳ መኾን አለበት” አያሌው ወንዴ (ዶ.ር)
Next articleበአማራ ክልል በድምቀት ለሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት በቂ የጸጥታ ስምሪት ማከናወኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።