
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጣና በዙሪያው ለሚገኙ ትላልቅ እና ትናንሽ ከተማዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ይሰጣል። 400 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው በሐይቁ ዳርቻ የተጠመጠመው የገጠሩ ነዋሪም የኑሮው መሰረት ከሐይቁ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። የሀገሬው የመጠጥ ውኃ፤ አሳ፣ ግብርና፣ መዝናኛው እና ጥበቡም ኹሉ የሚቀዳው ከጣና ነው። ሐይቁ የበርካታ ደሴቶች ባለቤት ነው። ደሴቶች ደግሞ ረጅም እድሜ እና ታሪክን አጭቀው የያዙ የገዳማት ማኅደርም ናቸው። ጣና ታሪክም ሃብትም ነው። በጣና ብቻ የሚገኙ በርካታ ባለልዩ ጣዕም የአሳ ዝርያዎችን የያዘ ሐይቅም ነው።
ሐይቁ ከኢትዮጵያም ተርፎ ለአለም ሥነ ምሕዳራዊ ብዝሃነት ጠቃሚ መኾኑን ታምኖበት በዩኒስኮ የተመዘገበ የሁሉም ሃብት ነው። ስለዚህ በጣና ውስጥ ያለውን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም እና ሐይቁን ከጉዳት ለመጠበቅ የሁሉም ሰው ኀላፊነት ያስፈልጋል ማለት ነው።
የአማራ ክልል የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ.ር) ጣና ለኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ብርሃን ማመንጨትን ጨምሮ በርካታ ጥቅሞችን እየሰጠ ነው ብለዋል። በዙሪያው የሚገነቡ ትልልቅ የመዝናኛ እና የግብርና ልማቶች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።
ይኹን እንጅ ጣናን በዘላቂነት ከጉዳት የመጠበቁ ሥራ በሚፈለገው መልኩ እየተከናወነ አይደለም ብለዋል ዶክተር አያሌው። እንቦጭ አረምን ጨምሮ ሌሎች ሰው ሰራሽ አደገኛ ድርጊቶች የሐይቁን ዘላቂ ጤና እየተፈታተኑት ስለመኾኑ ገልጸዋል። እንደ ዶክተር አያሌው ገለጻ :-
👉 በባሕር ዳር እና ጎርጎራ በሐይቁ ውኃ ውስጥ ድንጋይና አፈር በማስገባት በጣና ላይ የሚገነቡ የልማት ሥራዎች እየተስተዋሉ ነው
👉 ጎንደር እና ባሕር ዳርን ጨምሮ በዙሪያው ከሚገኙ ከተሞች የሚለቀቅ ፍሳሽ ቆሻሻ እየበከለው ነው
👉 በየዓመቱ በከፍተኛነቱ አስደንጋጭ የኾነ ደለል ወደ ሐይቁ በመግባት እየሞላው ነው
👉 ኤሌክትሪክ የማመንጨት ተግባር በወንዞች ላይ መኾን ሲገባው ከሐይቁ ላይ ውኃ ተቀንሶ እየተካሄደ ነው
👉 ለተለያየ ተግባር ከሐይቁ የሚወጣው ውኃ በጥናት የተለየ ሳይኾን ብክነት የተሞላበት በመኾኑ ሐይቁ እንዲሸሽ እያደረገው ነው
👉 የሐይቁን ዳርቻ ተከትሎ በባሕር ሸሽ እርሻ ሰበብ የጣናን ገላ የሚሸነቁሩ አርሶ አደሮች ተበራክተዋል ብለዋል።
እነዚህ እና ለጣና ጠንቅ የኾኑ መሰል ተግባራትን ለመከላከል እርሳቸው የሚመሩት የአማራ ክልል የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ምን እየሠራ እንደሚገኝ ጠይቀናቸዋል። የእንቦጭ አረምን በተመለከተ በተለያየ ጊዜም እንደሚገለጸው በማሽን እና በሰው ኃይል የታገዘ ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑ ይነገራል። ሐይቁን ዘልቆ ለተመለከተ ግን አሁንም ድረስ በአረሙ ተውጦ ይስተዋላል።
ዶክተር አያሌው በሐይቁ ላይ የሚስተዋሉ ሰው ሰራሽ ጉዳቶች በማሕበረሰቡ የግንዛቤ ጉድለት እና ቸልተኝነት የሚከሰቱ ናቸው ብለዋል። ይኽንንም ለመቅረፍ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ወደ ጣና የሚገባውን ደለል ለመቀነስ በዙሪያው “አረንጓዴ ቀለበት” የተባለ አጥር አይነት የልማት ሥራ ለማከናወን ጥናት ተጠናቅቆ ለውሳኔ ወደሚመለከተው አካል መቅረቡን አመላክተዋል።
ዶክተር አያሌው:-
👉በጣና ዳርቻ የማልማት ፍላጎታችን የሐይቁን ዘላቂ ጤና የማይጎዳ መኾን አለበት ብለዋል።
👉 የሐይቅ ዳር ልማቶች ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ቢኾኑም ቀድሞ በተጠና መዋቅራዊ ፕላን መሰረት እንጅ በጥናት አልባ የመልማት ፍላጎት ተገፍተው መኾን የለበትም።
👉ጣና በለስ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት መነሳት ቢችል ለሐይቁ ጤና ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
👉 ሐይቁን ከብክለት የሚታደግ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት መከተል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ጣና በዳርቻው ሲያልፉ በዓይን እያዩ የሚሳሱለት ውብ ሐይቅ እንጅ ቆሻሻ ወደ ውስጡ እየወረወሩ የሚያቆሽሹት፣ ድንጋይ እና አፈር እየከተቱ የሚጋፉት መኾን የለበትም። አለም ሊያየው የሚጓጓለት ሃብታችንን ኅልውናውን ጠብቀን የበለጠ ዓይነ ግቡ በማድረግ የወጣቶች ሥራ እድል መፍጠሪያ፣ የሀገርም የኢኮኖሚ ምንጭ ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ ስለጣና ዘላቂ ደኅንነት የሚጨነቁ እና ሐይቁን ለማስዋብ የሚታትሩ አካላትን ማመስገን፣ የልጥ መንከሪያ ለማድረግ የሚዳዱትን ደግሞ ማረም ያስፈልጋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!