ላል ይበላ: ዳግማዊ እየሩሳሌም!

243

ወልድያ፡ ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢየሩሳሌም እስከ ኢትዮጵያ የተዘረጋው የእምነት እና የማንነት ወሰን ዛሬም ዘመናትን አስቆጥሮ እንኳን አልደበዘዘም፡፡

ታላቅ ሕዝብን የመምራት ፍላጎት፣ ሀገርን የማሻገር መሻት፣ ድንበር አልፎ ወሰን ጠልፎ የመተሳሰር ትጋት፣ ጥበብ፣ ትህትና፣ አመስጋኝነት እና ታታሪነት የሁለቱ ሕዝቦች ተመሳስሎዎች ሆነው እንደዘለቁ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ክርስትናን በሕገ ልቦና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል የተቀበለች የቃል ኪዳን ደሴት ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን መቀየር እንደምን ይቻላቸዋል” የተባለላት ኢትዮጵያ ክርስቶስን በስደት ዘመኑ በፍቅር የተቀበለች ሀገረ ሰላም ተደርጋም ትወሰዳለች፡፡

ኢየሩሳሌምም የአዳምን መሳት፤ የዓለሙን መጥፋት በደሙ ይሽር፤ በፍቅሩ ያድን ዘንድ የመጣውን የዓለም ንጉስ ክርስቶስ ኢየሱስን የተቀበለች የአዳም መዳን የተስፋው ምድር ናት፡፡ ቤተልሄም ያኔ ስለፍቅሩ፤ ላል ይበላ ዛሬም ስለክብሩ ይዘምራሉ፡፡ በቤተልሄም እረኞች፤ በላል ይበላ አማኞች “ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ” ሲሉ ያመሰግናሉ፡፡

በ15ኛው እና 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው ከገቡት የውጭ ሀገር ጎብኝዎች መካከል አልባሬዝ ተጠቃሽ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊያን ጥንታዊ ጥበበኞች የታነጹትን ግሩም እና እጹብ የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከተመለከተ በኋላ በአግራሞት “እኔ ያየሁትን ብናገር ማን ያምነኛል” ሲል ይገልጻል፡፡

የቅዱስ ላል ይበላ ውቅር አበያተ ክርስቲያናት እስካሁንም ድረስ ያልተስተዋለ አዲስ የኪነ-ህንጻ ጥበብን ለዓለም ያስተማሩ ኅያው ምስክሮች ናቸው፡፡

ዓለም ዛሬም ድረስ እንኳን ህንጻን ከመሰረቱ እንጂ ከጣሪያው ለመጀመር የሚያስችል የኪነ ህንጻ ጥበብን ምስጢር መላበስ አልተቻላትም፡፡ እናም የአልባሬዝ መደመም የሚገርምም፤ የማይጠበቅም አልነበረም፡፡

ላል ይበላ ዳግማዊ እየሩሳሌም የሚለውን መጠሪያ እንዴት ልታገኝ ቻለች ስንል የጠየቅናቸው የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላል ይበላ ገዳም ዓለም አቀፍ ቅርስ ዋና አሥተዳዳሪ መምህር አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ ታሪክ ጠቅሰው ዋቢ ነቅሰው ሲመልሱ በቤተልሄም ያለ በላል ይበላ የሌለ ምን አለ ይላሉ፡፡ ከልደቱ እስከ ጥምቀቱ፤ ከትንሳኤው እስከ እርገቱ ያለውን ታሪክ የሚያወሱ ቦታዎች ሁሉ በላል ይበላ ይገኛሉ ብለውናል፡፡

ከመቃብረ አዳም እስከ ቀራኒዮ፣ ከጎለጎታ እስከ ጎል፣ ከቤተልሄም እስከ ቤተ ማሪያም፣ ከማሜ ጋሪያ እስከ ዮርዳኖስ፣ ከደብረ ታቦር እስከ ደብረ ዘይት፣ ከቢታኒያ እስከ ገዳመ ቆረንጦስ በላል ይበላ ታንጸዋል የሚሉት መምህር አባ ጽጌ ሥላሴ፤ ቅዱስ ላል ይበላ ሀገረ እግዚያብሔር ኢትዮጵያን እንደ እየሩሳሌም ያደርገለት ዘንድ መጠየቁ ምላሽ የተሰጠበት ነው ብለዋል፡፡

ለረጂም ዘመናት የክርስቶስ ፍቅር እና ተዓምር የተገለጸባትን እየሩሳሌምን ለመጎብኘት ኢትዮጵያዊ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ለወራት ተጉዘው ወደ እየሩሳሌም ይሄዱ ነበር ይላሉ መምህር አባ ጽጌ። የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተገነቡት ለቅዱስ ላል ይበላ በተሰጠ ቃልኪዳን የኢትዮጵያዊያን በየዓመቱ የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስቀረት ታስቦ እንደሆነም አጫውተውናል፡፡

ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮም ኢትዮጵያዊያን ምዕመናን ከጎጃም፣ ከትግሬ፣ ከሽዋ ሰላሌ ከአራቱም አቅጣጫ በእግራቸው እየተጓዙ ወደ ላል ይበላ ይመጣሉ፡፡ “ሥሙ ያንተ ይሆናል፤ የምሠራው ግን እኔ ነኝ” የሚል ቃል ኪዳን የተሰጠው ቅዱስ ላል ይበላ የገነባቸው አብያተ ክርስቲያናት የእየሩሳሌምን ጉዞ አቃልለዋልና “ዳግማዊ እየሩሳሌም” የሚል ስያሜ እንደተሰጣት ነግረውናል፡፡

ከወትሮው ጎብኝዎች የማይነጥፍባቸው፣ ቱሪስት አይቶ የማይጠግባቸው እና ኢትዮጵያዊያን የሚያምኑባቸው የቅዱስ ላል ይበላ ውቅር አብያ ክርስቲያናት በተለይም በኢየሱስ ክርስቶስ እና በቅዱስ ላል ይበላ ይበልጡን ይደምቃሉ፡፡ በየዓመቱ ወደ ላል ይበላ የሚመጡ የሃይማኖቱ ተከታዮችም የክርስቶስን ልደት በእየሩሳሌም እንዳከበሩ ቆጥረው “በል ማረኝና ልግባ ሀገሬ፤ ቅዱስ ላል ይበላ የዋሻው ገበሬ” እያሉ ይመለሳሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ሮሃ፡ የጥበብ ማዕከል የጠቢባን ሀገር!
Next article“በጣና ዳርቻ የማልማት ፍላጎታችን የሐይቁን ዘላቂ ጤና የማይጎዳ መኾን አለበት” አያሌው ወንዴ (ዶ.ር)