ደብረ ሮሃ፡ የጥበብ ማዕከል የጠቢባን ሀገር!

108

ላልይበላ: ታኅሣሥ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለትን ፈልፍለው ዋሻ፤ ከተማን ቆርቁረው መናገሻ ማድረግ መለያቸው ነው፡፡ ሰውን ቀርጸው ንጉስ፤ ዓለትን አንጸው መቅደስ ማድረግን ተክነውበታል፡፡ ንጉስም ቅዱስም የሚቀዳባት ደብረ ሮሃ ቤተ ክህነት አቅኝ ቤተ መንግሥት ተቀኝ ኾነው ዘመናትን አሳልፈውባታል፤ ኢትዮጵያንም አጽንተውበታል፡፡

ጠቢብ እጆች እና ደግ ልቦች ያቆሟቸው አብያተ ክርስቲያናት ዘመናትን አልፈው ዛሬም ድረስ ተዓምራዊ ናቸው፡፡ ታይተው የማይጠገቡት፣ ተመርምረው የማያልቁት እና ተፈትሸው የማይታዎቁት አብያተ ክርስቲያናት ኢትዮጵያዊያን ያውም በዚያ ዘመን ሊገነቧቸው አይችሉም እስከመባልም ደርሰዋል፡፡

ጥበብን ከትህትና፣ እውቀትን ከልግስና፣ እምነትን ከመንፈስ እና ባሕልን ከቅድስና ጋር የተቸራቸው የያኔዎቹ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን ትተዋቸው ያለፉት አሻራዎች ዛሬም መነጋገሪያ ከመኾን አልፈው የዛሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን ሕልውና በቀደምቱ ጠቢባን አሻራዎች ዙሪያ የተመሰረተ ነው፡፡

በቅዱስ ላል ይበላ አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ከብበው ባሕልን፣ እምነትን እና ማንነትን በጥበብ እየገለጹ ህይዎታቸውን ከሚመሩ በርካታ ወጣቶች መካከል ስዓሊ ብርሃኑ ገብረ ጻዲቅ አንዱ ነው፡፡ ስዕሎቹን እንደ ቀደምት አባቶቹ ብራና ፍቆ ቀለም በጥብጦ የሚሠራው ሰዓሊ ቀለሞቹ በአካባቢው ከሚገኙ እጽዋት ተቀምመው የተዘጋጁ መኾናቸውን ነግሮናል፡፡ ቆዳ ፍቆ ብራና ለማዘጋጀትም የራሱ የኾነ የአሠራር ሂደት ስላለው እርሱን ከአባቶቼ ተምሬያለሁ ነው ያለን ፡፡

የሚዘጋጁት ስዕሎች በዋናነት ሃይማኖታዊ መሰረት ያላቸው ናቸው የሚለን ሰዓሊ ብርሃኑ ጥንታዊ የኢትዮጵያዊያንን ባሕል፣ ማንነት እና ማኅበራዊ መስተጋብሮች የሚያሳዩ ናቸው ብሎናል፡፡ ከስዕሎቹ ከሚያገኘው ገቢ ይልቅ በስዕሎቹ የሚሸጠው መልዕክት እንደሚያስጨንቀው የነገረን ሰዓሊው ኢትዮጵያን ለቀሪው ዓለም የሚያስተዋውቁ በመኾናቸው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ነግሮናል፡፡

በቅዱስ ላል ይበላ አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ በተለይም በልደት በዓል ከሚሸጡ ቅርጻ ቅርጾች መካከል ሃይማኖታዊ መልእክት እና ግልጋሎት ያላቸው ይበዛሉ፡፡ የብራና ላይ ጽሑፎች፣ የመስቀል ቅርጻ ቅርጾች እና ሌሎች ንዋየ ቅድሳት በብዛት ለጎብኝዎች በሽያጭ ይቀርባሉ፡፡

በሽያጭ ላይ ያገኘናቸው ቄስ ወልደ አማኑኤል የቤተሰቦቻቸውን ህይዎት የሚመሩት እና ቤታቸውን የሚደጉሙት ከቅርጻቅርጽ በሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ ነው፡፡

ቅርጻ ቅርጾቹን በመግዛት የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቀዳሚዎች ናቸው የሚሉት ቄስ ወልደ አማኑኤል የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም በተይም በልደት በዓል ሰሞን ከፍተኛ መጠን ያለው ግብይት እንደሚፈጽሙ ነግረውናል፡፡ የሚሸጡት ቀርጻ ቅርጾች እና የጥበብ ውጤቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ እና ስለእምነታቸው የሚመሰክሩ ትርጉም ያላቸው ናቸው ብለውናል፡፡

በላል ይበላ ከተማ የሚከበረውን የልደት በዓል ምክንያት አድርጎ በተከፈተ ባዛር የሀገር ውስጥ ምርቶችን እና አልባሳትን ለእንግዶች ስትሸጥ ያገኘናት ወጣት መቅደስ አማረ ሥራዎቿ ኢትዮጵያን የሚመስሉ እና ጥንታዊነቷን የሚመሰክሩ የጥበብ ውጤቶች ናቸው ብላናለች፡፡ አልባሳቱ የሀገር ውስጥ ግብዓትን የሚጠቀሙ ናቸው ያለችን መቅደስ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በብዛት እንደሚገዙም ነግራናለች፡፡

የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ዓለም አቀፍ ቅርሶች በዚህ መኖራቸው ላል ይበላ ከተማን ሙሉ በሙሉ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተች ከተማ እንድትኾን አድርጓታል ብለውናል፡፡ አስተያየት ሰጭዎቹ የጥበብ ማዕከል የጠቢባን ሀገር በኾነችው ደብሮ ሮሃ የሚገኘውን ይህንን ምድራዊ ጸጋ እና ሰማያዊ በረከት የቱሪስት መዳረሻ መጠበቅ እና ማስተዋወቅ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው ላገለገሉ አምባሳደሮች ምስጋና አቀረቡ።
Next articleላል ይበላ: ዳግማዊ እየሩሳሌም!