ተስፋን ያነገበው የመገጭ ግድብ ሥራ

214

ጎንደር፣ ታኅሣሥ 25 ፣ 2015 (አሚኮ) ለጥም ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ፣ ለዓመታት የሚናፈቅ፣ የውኃ ግድብ ነው፣ ውኃ ግን የለውም፣ ለጥም ማርኪያ ተጠብቋል፣ በተጠበቀው ጊዜ ግን አልደረሰም። የታሪካዊቷን ከተማ ሕዝብ ውኃ ያጠጣል፣ በዙሪያው የሚገኙ አርሶ አደሮችንም በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ነበር። ዳሩ እስካዛሬ ድረስ ነበር ብቻ ነው። የሚጠናቀቅበት፣ ተስፋው እውን የሚኾንበት ጊዜ በውል አልታወቀምና።

የመገጭ ግድብ ውል ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ሦስት ጊዜ ምርጫ አከሂዳለች፣ በሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ተመርታለች። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። ያልታሰቡት ኾነዋል። ያልተገመቱት ተደርገዋል። አይኾንም የተባለው ኾኗል። አያሌ የደስታ፣ አያሌም የሀዘን ጊዜያት አልፈዋል። ብዙ ነገሮች ሄደው እልፍ ነገሮች መጥተዋል። በመገጭ ሰማይ ሥር ግን ከዓመታት መንጎድ ውጭ የተለወጠ ነገር የለም።

የመገጭ ግድብ ውል ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ የአማራ ክልል በስድስት ርእሳነ መስተዳድሮች ተመርቷል፣ የመገጭ ግድብ ውል ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ግደቡ የሚገነባባት ከተማ ጎንደር በስድስት ከንቲባዎች ተመርታለች።
ግድቡ ተጀምሮ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ ከሦስት እጥፍ በላይ ዘግይቷል። ሲጀመር ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር። ነገር ግን ዛሬም ድረስ ሳይጠናቀቅ ቀጥሏል። መገጭ ተስፋ የሞላው፣ ውኃ የሌለው ግድብ ኾኗል።

የመገጭ ግድብ ግንባታ ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጂነር ወርቅነህ አሰፋ የግድቡ ውል የተፈረመው እ.አ.አ መስከረም 2008 እንደነበር አስታውሰዋል። ውሉ ከተፈረመ በኋላም ለዓመታት በበጀት እጥረት ቆሞ መቆየቱንም ተናግረዋል። ከዓመታት መዘግየት በኋላ በ2013 ግንባታው መሬት ላይ መውረዱን ያስታውሳሉ። ከ2013 ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙት መምጣታቸውንም ገልጸዋል። የበጀት እጥረት፣ የወሰን ማስከበር፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የስሚንቶ እጥረት እና ሌሎች ችግሮች ደግሞ ለግድቡ መዘግየት የሚነሱ ችግሮች ናቸው።
ግድቡ ዓመታትን ተጀምሮ በማሳለፉ በተሠራው ሥራ ላይ ሌላ ችግር መፈጠሩንም ተናግረዋል። የተሠራው ሥራም የመንሸራተት ችግር ገጥሞት ነበር። አሁን ላይ የመንሸራተት አደጋውን በተለያዩ ባለሙያዎች በማስጠናት ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት።

መገጭ 185 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ የመያዝ አቅም አለው። 116 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ የሚኾነው ለመስኖ አገልግሎት ይውላል፣ 32 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ የሚኾነው ለንፁሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ሲውል 19 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ የሚኾነው ደግሞ በግድቡ ውስጥ ይተኛል፣ ቀሪው ይተናል። ውኃው የሚተኛበት ደግሞ ከ3 እስከ 5 ኪሎሜትር ስፋት ይሸፍናል። አሁን ላይ የግንባታ ፍጆታቸው ከፍ እያለ በመሄዱ የቀድሞውን ጨምሮ 6 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል። በኢትዮጵያ አቆጣጠር ግድቡ ሰኔ 2016 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞለት የነበረ ቢኾንም ተጨማሪ ጥናት ተደርጎበት በ2017 ዓ.ም ዋና ዋና ሥራዎች እንዲጠናቀቁ፣ በ2018 ዓ.ም እስከ ሕዳር መጨረሻ ድረስ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እንዲጠናቀቁ እቅድ ተይዞለታል ነው ያሉት።

በተያዘው እቅድ መሠረት 2017 ዓ.ም ለንፁሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ይሰጣልም ብለዋል። አሁን ላይ ችግሮቹ ተለይተው ታውቀዋል ያሉት ተጠሪ መሐንዲሱ በሦስት ዓመታት ለማጠናቀቅ በቀን 16 ሰዓታት ለመሥራት ግድ እንደሚልም አንስተዋል። አሁንም የካሳ ክፍያው ከፍተኛ መኾንና የምንዛሬ መጨመር ለፕሮጀክቱ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

በግድቡ ላይ ይነሱበት የነበረው የጥራት ችግር በጥናት ተመልሷልም ነው ያሉት። ግድቡ በጥንቃቄ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ሁሉም የሚጠበቅበትን በመወጣት ፕሮጀክቱን ለአገልግሎት ማብቃት ይገባልም ነው ያሉት። የመገጭ ግድብ ሲጠናቀቅ ለመጠጥና ለመስኖ አገልግሎት ከመዋሉም በላይ ለአሳ እርባታ ጠቃሚ ይኾናል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ነገሥቱ የተመላለሱበት፣ አፄ ቴዎድሮስ የተማሩበት”
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው ላገለገሉ አምባሳደሮች ምስጋና አቀረቡ።