“ነገሥቱ የተመላለሱበት፣ አፄ ቴዎድሮስ የተማሩበት”

164
Made with LogoLicious Add Your Logo App
ጎንደር: ታኅሣሥ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ራእይ የተቀቡት፣ ለንግሥና የተመረጡት፣ ለልእልና የታጩት፣ አንድ ኾነው ሳለ እንደ ሺህ የተጠሩት፣ አንድ ኾነው ተነስተው፣ ብዙዎችን እፍርተው፣ ጀግኖቹን አስከትለው አንድ ያደረጉት፣ በወዳጅ የተከበሩት፣ በጣለት የተፈሩት፣ የተበተነ የመሠለውን የሰበሰቡት፣ የራቀውን ያቀረቡት፣ አቅም ያጣውን ጉልበት የኾኑት፣ በሀገርና በሠንደቅ ላይ የተነሳውን የቀጡት ተምረውበታል።
ከመርጌታው እግር ሥር ተቀምጠው ፊደል ቆጥረውበታል፣ አቡነ ዘበሰማያት፣ ዳዊት ደግመውበታል፣ ምስጢር አይተውበታል። ምስጢራትንም መርምረውበታል።
በኢትዮጵያ ኾነው ኢየሩሳሌምን ነፃ ለማውጣት የናፈቁት፣ የአባቶቻቸውን ዙፋን ወደ ክብሩና ወደ አስፈሪነቱ የመለሱት፣ ለሀገር ክብር ኖረው፣ ለሀገር ክብር ያለፉት፣ ድል እንጂ ሽንፈት የማያውቁት ታላቁ ሰው ራእይ ሰንቀውበታል፣ የጥበብን መንገድ አይተውበታል፣ ፈጣሪን መፍራት፣ ሰውን ማክበር ተምረውበታል። ታላቅ የመኾን ሕልም ቋጥረውበታል።
በቀን እና በሌሊት በአጸዱ ሥር እየተመላለሱ አገልግለውበታል፣ በደጀ ሰላሙ አድረውበታል፣ በአጸዱ ሥር ባሉ ጥሻዎች እየተመላለሱ መንፈሳዊ አበው ጋር ኖረውበታል፣ የአበውን ጉልበት እየሳሙ፣ እግር እያጠቡ፣ ለአበው እየታዘዙ ተመርቀውበታል፣ ይቅናህ ታላቅ ሁን ተብለውበታል። ከሚወዷቸው እናቱ ጋር ተለይተው፣ በናፍቆት ውስጥ ኾነው በድንጋይ እየተቀመጡ እውቀትን ገበዩ። የገበዩዋት እውቀትም ሃይማኖትን የምታፀና፣ ለአንድነት የቆመች፣ ለፅድቅ የበረታች፣ ለክብር የተመረጠች ነበረች። በአፀዱ ሥር እየተመላለሱ በተማሩበት በዚያ ዘመን አበው ታላቅ እንደሚኾኑ ይናገሩ ነበር። የቀለም አቀባበላቸው፣ ስርዓትና ሕልማቸው ሁሉ ታላቅ ስለመኾናቸው አስቀድሞ ይናገር ነበርና።

ከጀግኖች ሀገር፣ ከልበ ሙሉዎች ምድር፣ ከጣና ዳር ደምቢያ ደርሻለው። ደምቢያ ጣና ያሳመረው፣ ፈጣሪ እንደ መዳፍ አለስልሶ የፈጠረው፣ ፀጋና በረከትን የቸረው ምድር ነው። በደምቢያ አያሌ ታሪኮች፣ አያሌ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሥፍራዎች ሞልተዋል። ከበዙት ታሪካዊ ሥፍራዎች መካከል ካሳ የተማሩበትን፣ ፊደል የቆጠሩበትን፣ ምስጢር ያመሴጠሩበትን ታላቅ ደብር አይ ዘንድ ወድጃለሁ። ታሪክ የበዛበት፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ያሉበት፣ ቴዎድሮስ የተማለለሱበት ነውና ለማየት ጓጉቻለሁ።
ጀምበር በማለዳ በጣና ሐይቅ ላይ ብርሃኗን ጥላለች። ከሐይቁ ጋር የፈጠሩት ኅብረት ለምድር ልዩ ውበት ኾኗታል። አረንጓዴ ካባ የለበሰው የደምቢያ ምድር ተውቧል። ጀምበር በማለዳ ለምድር የሰጠችውን ውበት እያደነኩ ከጯሂት ወደ ጎርጎራ የሚወስደውን መንገድ ይዤ ተጓዝኩ። ጥቂት እንደሄድኩም ወደ ምሥራቅ ንፍቅ ታጥፌ በጠጠር መንገዱ ገሰገስኩ። የቀዬው ገበሬዎች በማለዳ ወደ ሥራ ወጥተዋል። እረኞች ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ግጦሽ ወርደዋል። በቀኝና በግራ የሚታየው ሁሉ ሀሴትን ይሰጣል። በቀጭኗ መንገድ እየገሰገስኩ ነው። መንገዴ ሩቅ እንዳልኾነ ሰምቻሉ።
የማለዳው ድባብ ሳይጠፋ ልቤ ከከጀለው ሥፍራ ተቃርቤያለሁ። ልቤ ያርፍበት ዘንድ የወደደው ታላቁ ሥፍራ በአሻገር ይታይ ጀምሯል። ያ ታላቅ ሥፍራ ረጃጅም ዛፎች ከበውታል። በሕብረትም ዙሪያውን አሳምረውታል። ገና በአሻገር ሲታይ ግርማው አስፈሪ ነው። ልቤ ሀሴትን እያደረገች ወደ ባለ ግርማው ሥፍራ ተጠጋሁ።
እንደ መዳፍ በለሰለሰው ሀገር፣ ከጣና አጠገብ ባለው ሜዳማ ምድር፣ ደምቢያ በተሰኘ ድንቅ ሥፍራ ቸር እና ገር የተሰኙ ሁለት ወንድማማቾች ይኖሩ ነበር። እነዚህ ወንድማማቾችም የቀዬው ባላባቶች ነበሩ። በሰፊው እርስታቸው እያረሱ እና እያፈሱ፣ ሲሻቸው ከወተቱ እንዲያም ሲል ከማሩ እየተጎነጩ ይኖሩ ነበር። በዚያም ዘመን አፄ አምደጽዮን ነግሠው ነበር። ንጉሡም በጣና ሐይቅና በጣና ዳርቻ አድባራትን ይደብሩ፣ ገደማትን ይገድሙ ነበር። አፄውም ወደ ደምቢያ በሄዱበት ጊዜ ቸር እና ገር የተሰኙትን ሁለቱን ወንድማማቾች አገኟቸው። ንጉሡም የእነዚያን ባላበቶች ስም ጠየቁ። ቸር እና ገር እንባላለን አሏቸው። በስማቸውም ተደነቁ። ንጉሡም በሉ ከዚህ ወዲያ የዚህ ቦታ መጠሪያው ቸርገር ይሁን አሉ ይባላል። የጥንተዊው የቸርገር ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አገልጋይ እና ታሪክ አዋቂ ቄስ መላክ አሻግሬ እንደነገሩኝ በዚያ ሥፍራም አምደጽዮን የማርያምን ቤተመቅደስ አሠሩ። ዘመናትም ነጎዱ።
ንጉሡ በሁሉቱ ወንድማማቾች ስም የተሰየመው ያ ሥፍራ በተለምዶ ቸንከር ይሉታል። ትክክለኛ ስሙ ግን ከጥንት የቆዬው ቸርገር ነው ብለውኛል ቄስ መላክ። በዚያ በለሰለሰ የደምቢያ ምድር ላይ አቸራ ተክለሃይማኖት የሚባል ደብር ነበር። አምደጽዮን ያሰሯት ቸርገር ማርያም ደግሞ በቸርገር ነበረች። በአንድ ወቅትም እቴጌ ሐመልማለወርቅ ድንቅ ነገር በራእይ ታያቸው። በታያቸው ራእይም አቸራ ተክለሃይማኖትን ወደ ቸርገር ማርያም፣ ቸርገር ማርያምን ወደ አቸራ ተክለሃይማኖት ወስደው አቀያሯቸው። ቀድሞ አቸራ የነበረው ተክለሃይማኖት ቸገር መጣ። አምደጽዮን በቸርገር ያሰሯት ማርያምም ወደ አቸራ ሄደች።
ቸገር ተክለሃይማኖት አጸድ ሥር ነኝ። ረጃጅም እፅዋት፣ በእፅዋቱ ላይ የሠፈሩ አእዋፋት ዝማሬ፣ በአጸዱ ሥር የሚያዜሙ ተማሪዎች ልሳን ሀሴት ይሰጣል። ዓይኔን በቀስታ እያማተርኩ ተመለከትኩ። አብዝቼ ደስ አለኝ። ጂግራና ቆቅ የሚመላለሱባቸው በሚመስሉ ቀጫጭን የአፀድ ሥር መንገዶች በቀስታ እየተመላለስኩ በአምሳለ መስቀል የተሠራውን ታላቅ ደብር ተመለከትኩት። ደብሩ የበዙ ታሪኮች የተሠሩበት፣ ፃድቃን የወጡበት፣ ሊቃውንት የፈለቁበት፣ አሁንም የሚፈልቁበት ነው። የዚያኔውን ልጅ ካሳ የኋለኛውን ቴዎድሮስ በአጸዱ ሥር የተመላለሱበት ነውና ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዤ እግራቸው በረገጠበት ሥፍራ ተመላለስኩ። እንደ እርሳቸው ሁሉ በረጃጅም ዛፎች ግረጌ ተዘዋወርኩ። ድንቅ ነገር ተመለከትኩ።
ቤተክርስቲያን በጠላቶች በተፈተነችበት ዘመን ካህናቱ ታቦታትን እያመጡ በቸርገር ተክለሃይማኖት መቅደስ ያስቀምጡ ነበር። የመከራ ዘመን መውጫ የነበረ፣ ጠላት የማይዳፈረው፣ ጠላት በመጣ ጊዜ ንቦች ወጥተው የሚናደፉበት፣ በአምላክ ትእዛዝ እንደ መላእክት እየተፋጠኑ የሚጠብቁት፣ ከማንም ከምንም የማያስነኩት ታላቅ ደብር ነው።
Made with LogoLicious Add Your Logo App
በዚህ ሥፍራ የአትጠገብ አንድያ ልጅ የቀድሞው ካሳ፣ የኋለኛው ቴዎድሮስ፣ አባ ታጠቅ ፣ መይሳው ተምረውበታል። እሳቸው ቁጭ ብለው ከአበው ፊደል የቆጠሩባት ዋርካ ዛሬም ድረስ በቸርገር ተክለሃይማኖት ትገኛለች። ያቺ ዋርካ የታደለች ናት አበው ሊቃውንት ከሥሯ ተምረውባታል፣ ጳጳሳት ወጥተውባታል፣ ንጉሥ ተገኝቶባታልና። ዋርካዋስ ታድላለች ካሳን አስጠልላለች፣ የካሳን ታሪክ ስትመሰክር ትኖራለች። ካሳ ከተማሩባት ዋርካ ሥር ቆሜ ካሳን ያየኋቸው፣ ከአጠገባቸው የቆምኩ እስኪመስለኝ ድረስ በሀሳብ ወደ ኋላ ተጓዝኩ። ዳሩ ካሳና ሌሎች ተማሪዎች የተቀመጡባቸውን ሥራዎች እንጂ ካሳን ማየት አይቻልም።
የቀድሞው ልጅ ካሳ የኋለኛው ቴዎድሮስ በቸርገር ተክለሃይማኖት ዲያቆን ኾነው እንደቀደሱበት፣ በኋላም መልከ መልካሟን ባለ ብልኋን ተዋበችን ባገቡ ጊዜ ስጋ ወ ደሙ እንደተቀበሉበት፣ ታላቁን ሥርዓትም እንደፈፀሙበት ቄስ መላክ ነግረውኛል። ካሳ በቸርገር ተክለሃይማኖት በነበሩበት ጊዜ አያሌ ነገሮችን አይተዋል። ለሀገራቸው አንድነት፣ የጠነከረ የአስተዳደር ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ተመልክተውበታል። ያ በልጅነት ዘመናቸው በቸርገር ተክለሃይማኖት አጸድ ሥር በነበሩበት ዘመን በመሳፍንቱ ያዪት ያልተገባ ነገር ካሳ
በጥንካሬ እንዲነሱ፣ በራእይ እንዲገሰግሱ አድርጓቸዋል ይባላል።
ዘመን ዘመን እየገፋ ሆዶ የመሀዲስቶች ጦር አብያተክርስቲያናትን እያቃጠለ፣ ካህናትን እና መነኮሳትን፣ ዲያቆናትን እና አንባቢያንን እየገደለ፣ ገዳማትን እያጠፋ መጣ። ለሃይማኖታቸው ቀናኢ የነበሩ አበው ስለ ሃይማኖት ሰማእትነትን ተቀበሉ። ከሚቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ጋር ተቃጠሉ። ያ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን የሚያቃጥለው የመሀዲስቶች ጦርም ደምቢያ ቸርገር ተክለሃይማኖት ደረሰ። የድርቡሾች ጦርም ያቃጥለው ዘንድ ወደ አጸዱ ቀረበ። በዚያን ጊዜ ከወተት የነጣ የንብ መንገዳ ከጉልላቱ ላይ ወጥቶ ጦረኛውን ከነፈረሱ ነደፈው፣ መውጫ እስኪጨንቀው ድረስ ያ ቤተክርስቲያን ሊያቃጥል የመጣ ጦረኛ ሸሸ። ፈረስ ሜዳ ከሚባል ሥፍራም ሊቃጥሉ የመጡ ድርቡሾች እስከ ፈረሶቻቸው አለቁ ይባላል።
ያም ንብ ዛሬም ድረስ በደብሩ አለ። እኔም በአጸዱ ሥር ንቡን ባየሁ ጊዜ ልቤ ተሸበረች። የንብ መንጋው ይሰፍርብኝ፣ ከተቀደሰው ስፍራ ከእነ እድፍህ ገብተሃልና ብሎ ይቀጣኝ ይኾን እያልኩ ፈራሁ። ራድኩ። ንቡ በመስቀል ቅርፅ በተሠራው ደብር በአራቱም ንፍቅ ኾኖ ዛሬም ተልእኮውን ይፈፅማል። ቤተክርስቲያኑን ለመተናኮል የመጣን ሰው ይቀጣል፣ በካህናቱ መካከል ቂም ከተፈጠረ ወደ ቤተመቅደስ እንዳይገቡ ይከለክላል፣ ሰዓት እላፊ ቅዳሴ ለመግባት ሲመጡም አያስገባም ነው ያሉኝ ቄስ መላክ።
የመሐዲሲቶች ጦር አብያተክርስቲያናትን እና ገዳማትን እያጠፋ በመጣ ጊዜ አርባ አራት ታቦታት በቸርገር ተክለሃይማኖት ቤተ መቅደስ ተቀምጠው ነበር። ካህናቱ ታቦታትን እየያዙ ቸርገር ተክለሃይማኖት ይጠለሉ ነበር። በኋላም ድርቡሽ ተሸንፎ ሕዝቡም ሰላማዊ ኖሮ መኖር ሲጀምር ታቦታቱ እየወጡ ቤተ መቅደስ እየታነፀላቸው ወደ ቀደመ ሥፍራቸው ተመለሱ ብለውኛል ቄስ መላክ። ከ1952 ዓ.ም ጀምረው በዲቁና ከዚያም በቅስና እያገለገሉ ያሉት የቸርገር ተክለሃይማኖት ገበዝ ቄስ መላክ አካለብርሃንም ቸርገር ተክለሃይማኖት ታላላቆች የተገኙበት፣ ነገሥታት፣ መኳንንት እና መሳፍንት የተማሩበት ታላቅ ሠደፍራ መኾኑንም ነግረውኛል።
Made with LogoLicious Add Your Logo App
በዚያ አጸድ ሥር የቴዎድሮስ የዘውድ መደገፊያ፣ አስደቅድቀን የተሰኘ ጠመንጃ፣ ከኮሶ እንጨት የተሠራ ስማ ጎንደር የተሰኘ ከበሮን ጭመሮ የከበሩ እንቁዎች አሉበት። ቸርገር ታላቁ ደብር፣ ቸርገር ተክለሃይማኖት ታላላቆቹ የተገኙበት፣ ሊቃውንቱ እንደ ምንጭ የፈለቁበት፣ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ እጅ የነሱለት። በአጸዱ ሥር ኾነው ጸሎት ያደረሱበት ሥፍራ ነው።
የምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ባሕል ቱሪዝም እና ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋሴ አስናቀው ቤተክርስትያኑ ባለው ታሪክ ልክ እየለማ አለመኾኑን ተናግረዋል። የቱሪስት መዳረሻ ይኾን ዘንድ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልፀዋል። ጎብኚዎች ታላቁን ሥፍራ እንዲጎበኙትም ጥሪ አቅርበዋል።
በታላቁ ሥፍራ ብዙ ነገር አየሁ። ብዙም ሰማሁ። በሰማሁትና በአየሁትም ሁሉ ተደነቅኩ። ቸርገር ተክለሃይማኖት የእልፍ ታሪኮች ባለቤት።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ጎርጎራ ማን አገኘሽ? ማን ደበቀሽ? ማንስ አየሽ?”
Next articleተስፋን ያነገበው የመገጭ ግድብ ሥራ