“እንግዶቻችን እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ያለምንም ስጋት እና ጉድለት በዓሉን በደስታ አክብረው ይመለሳሉ” መምህር አባ ጽጌ ስላሴ መዝገቡ

131
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ንግስናን ከቅድስና አስተናብረው የመሩት ጥንታዊ ነገስታት መናገሻ፤ የክርስቶስን መወለድ ለሚሹ ክርስቲያኖች መዳረሻ ናት ጥንታዊቷ ደብረ ሮሃ፡፡ የንጉሷንም የቅዱሷንም ልደት በአንድ የምታከብረው ላሊበላ በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ “ዳግማዊት ኢየሩሳሌም” የሚል መጠሪያ ተችሯታል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ጥንታዊ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ልደት ለማክበር በየዓመቱ ወደ እየሩሳሌም ይጓዙ እንደነበር ይነገራል፡፡ ያ ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ውጣ ውረድ እና መከራ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ጥበብ እስኪታነጹ ድረስ የቀጠለም ነበር፡፡
የክርስቶስን ልደት በእየሩሳሌም ለማክበር ወደ ቦታው ከሚያቀኑት መናንያን እና መንፈሳዊያን መካከል ቅዱስ ላል ይበላ አንዱ ነበር ያሉን የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላል ይበላ ገዳም ዓለም አቀፍ ቅርስ ዋና አሥተዳዳሪ መምህር አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ የኢትዮጵያዊያን እየሩሳሌምን መሻት በቅዱስ ላሊበላ ጥረት በኢትዮጵያ እውን ሆኗል ይሉናል፡፡
ልደትን በላሊበላ ማክበር ለክርስቲያኖች በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው የሚሉት የገዳሙ ዋና አሥተዳዳሪ ልደቱ በፈጣሪው ልደት ቀን የሚከበረው ቅዱስ ላሊበላ ልደትም አብሮ ይከበራል ብለውናል፡፡ በዓሉ ለዘመናት ከመላው ዓለም እና ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በሚመጡ በርካታ ምዕመናን በድመቀት ሲከበር ቆይቷል ነው ያሉን፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እስከ ተደጋጋሚ ጦርነት የበዓሉን ድባብ አቀዛቅዞት ቢቆይም በፈጣሪ ተዓምር ክብረ በዓሉ ሳይስተጓጎል ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ በዓሉን በላሊበላ አለመታደማቸው በተለይም በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ መቆየቱን መምህር አባ ጽጌ ሥላሴ ነግረውናል፡፡
በኢትዮጵያ የሰፈነው አንጻራዊ ሠላም የ2015 ዓ.ም የልደት በዓልን በደብረ ሮሃ በድመቀት ለማክበር እድል ሰጥቶናል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው “እንግዶቻችን እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ያለምንም ስጋት እና ጉድለት በዓሉን በደስታ አክብረው ይመለሳሉ” ነው ያሉት፡፡ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀው እንግዶችን መቀበል መጀመራቸውንም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
ልደትን በላሊበላ መታደም መንፈሳዊ በረከትን ብቻ ሳይሆን ሰዋዊ ሃሴትንም ያጎናጽፋል ያሉት የገዳሙ ዋና አሥተዳዳሪ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም የሚገኙ ወገኖች ወደ ቅዱስ ላሊበላ መጥተው የእየሰሱ ክርስቶስንም የቅዱስ ላሊበላንም የልደት በዓል በጋራ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምድር የሰጠችን እምቅ ሃብት! – ማዕድን
Next article“ጎርጎራ ማን አገኘሽ? ማን ደበቀሽ? ማንስ አየሽ?”