ምድር የሰጠችን እምቅ ሃብት! – ማዕድን

320
ደብረ ብርሃን፡ ታኅሣሥ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ከሚገኝባቸዉ አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡
በክልሉ የዓባይ ሸለቆን እና በሰሜን ሸዋ ዞን የጀማ ተፋሰስን ተከትሎ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለተለያዩ ተግባራት የሚውሉ በርካታ የማዕድን ሃብቶች መኖራቸውን የክልሉ የማዕድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡
በጀማ ተፋሰስ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል ደግሞ የእንሳሮ ወረዳ አንዱ ነው። የወረዳው ማዕድን ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘሪሁን ገንዘብ፤ በወረዳ ካሉት 14 ቀበሌዎች ውስጥ 13 የማዕድን ክምችት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኖራ ድንጋይ ፣ጅብሰም ፣የግንባታ አሸዋ ፣የግንብ ድንጋይና ሲልካ በወረዳው በስፋት ከሚገኙት ማዕድኖች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው። በተለይም ለላርጎ፣ ለመሥታዎት፣ ለቢራ ጠርሙስ እና ለመሳሰሉ 17 አይነት ምርቶች መሥሪያ የሚውለው የሲልካ ሳንድ በስፋት ይገኛል።
ድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ፣ አምበር፣ ኦፓል፣ ብረትና ነሐስ የመሳሰሉ ማዕድናት ደግሞ በጥናት ላይ ይገኛሉ። ለወረዳው ትኩረት ተሰጥቶት ጥናት ቢደረግ በርካታ ማዕድናት ሊገኝበት እንደሚችልም ነው ያነሱት።
አሁን ላይ በወረዳው፦
✍️ ከ4 ሚሊዮን በላይ ቶን የሲልካ ሳንድ
✍️ ከ2 ሚሊዮን በላይ ቶን የኖራ ድንጋይ
✍️ ከ1 ሚሊዮን በላይ ቶን የጂብሰም ክምችት በጥናት ተረጋግጦ በባለሃብቶች በመልማት ላይ ይገኛል።
በወረዳው አኹን ላይ 12 ፋብሪካዎች በግንባታና በሥራ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ሲልካ ሳንድ እያመረቱ ለብርጭቆና ለመሥታውት አምራች ፋብሪካዎች እያቀረቡ የሚገኙ ናቸው። የመሥታዎት ፋብሪካ ለመገንባት ማስፋፊያ የጠየቁ እንዳሉም ገልጸዋል። ወረዳው ማልማት ለሚፈልግ ባለሃብት ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል።
በሲልካ ማዕድን ልማት ፈቃድ ወስደው በማምረት ላይ ያገኘናቸው ታምራት ተሾመ እንዳሉት በወረዳው የሚገኘውን ሃብት በማበጠርና በማጠብ ደብረ ብርሃን ለሚገኝ ብርጭቆ አምራች ፋብሪካ ሲልካ ያቀርባሉ። ከ50 በላይ ለሚኾኑ ሰራተኞችም የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። በቀጣይ በቀን እስከ 15 ሲኖ ትራክ የጭነት መኪና ሲልካ ለማምረት አቅደዋል። ድርጅቱ ፕሮሰስ ከማድረግ አልፎ የብርጭቆ ፋብሪካውን በወረዳው ለመትከል ማቀዱንም ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ማዕድን ሃብት ልማት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ በሱፈቃድ ዘየደ በዞኑ 21 የማዕድናት አይነቶች መለየታቸውን ነግረውናል።
በተለይም ደግሞ አንኮበር፣ እንሳሮ፣ መረሃ ቤቴ፣ መንዝ ጌራና ምንጃር ሸንኮራ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያለባቸው ወረዳዎች መኾናቸውን አንስተዋል። በሚዳ ወረሞ፣ እንሳሮና መርሃ ቤቴም ላይ ሰፊ የኾነ የኖራ ድንጋይና የሲልካ ሳንድ ክምችት መኖሩን ለአብነት አንስተዋል።
ማዕድን መኖሩ በተረጋገጠባቸው ወረዳዎችም ፈቃድ ወስደው በማምረትና ወደ ምርመራ ሥራ የገቡ ባለሃብቶች እንዳሉም ገልጸዋል። በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በሴራሚክ ማምረት፣ በአንኮበር ወረዳ ደግሞ ሦስት ባለሃብቶች በድንጋይ ከሰል ፈቃድ ወስደው የምርመራ ሥራ እየሠሩ ነው።
በዞኑ የክምችት መጠናቸው ያልታወቀ እንደ ብረትና ቢንቶናይት የመሳሰሉ ማዕድኖች መኖራቸውን አስረድተዋል።
መምሪያው ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና ከክልሉ በተቋቋመው የጥናት ቡድን ጋር በመኾን በአካባቢው ባለሙያዎች የሚቀርቡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ጥናት ለማካሄድ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት፦
. የጥናት
. ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርና
. ራሱን የቻለ ተቋም አለመዋቀር ችግሮች እንደነበሩ ገልጸዋል።
አኹን ላይ ዞኑ ሕገ ወጥ የማዕድን ዝውውርን የመከላከልና የማዕድን ሃብት ለሀገር ያለውን ጠቀሜታና ለሥራ ዕድል ያለውን አቅም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑ ተነስቷል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በመስኖ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ
Next article“እንግዶቻችን እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ያለምንም ስጋት እና ጉድለት በዓሉን በደስታ አክብረው ይመለሳሉ” መምህር አባ ጽጌ ስላሴ መዝገቡ