“በመስኖ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

153
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመስኖ ከሚለማ ስንዴ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል። በ2015 ዓ.ም ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ይሸፈናል። 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎም ታቅዷል። በሥራው ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፉበታል።
አርሶ አደር መንግስቱ ዘለቀ በባሶ ሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ ስንዴ በበጋ ሲዘሩ ሁለተኛ ዓመታቸው ነው። በ2014 ዓ.ም ከአንድ ሄክተር መሬት 50 ኩንታል ስንዴ አግኝተዋል። ዘንድሮ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር አላጋጠመኝም ብለዋል። በወረዳቸው የስንዴ የዘር ብዜት መኖር ምርጥ ዘር በቅርቡ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። በአካባቢው ስንዴ በበጋ የማምረት ልምድ የተጀመረው በቅርቡ ቢኾንም በዚህ ዓመት በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ስንዴ ዘርተዋል። ከ80 ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ማቀዳቸውን ነው የነገሩን።
በምግብ ራስን ለመቻል አርሶአደር መንግሥቱ የባህር ዛፍ ችግኛቸውን አፍልሰው ስንዴ እንደዘሩ ነው የተናገሩት። ሌሎች አርሶ አደሮችም የእሳቸውን ፈለግ ቢከተሉ ከገባንበት ችግር በአጭር ጊዜ እንወጣለን ብለዋል። የማዳበሪያ ችግር ከተፈታ እና የውኃ አማራጫቸው ወንዝ በመኾኑ የነዳጅ እጥረት መፍትሔ ካገኘ ውጤታማ እንደሚኾኑ ተናግራዋል።
ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ጌቴ ተሾመ ሁለት ተኩል ገመድ መሬታቸው ላይ ስንዴ ለመዝራት አቅደዋል። አንድ ሄክታር መሬት በዘር ሸፍነዋል። ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ገዝተዋል። የባለሙያ ድጋፍም አልተለያቸውም። የመንግሥት የተጠናከረ ድጋፍም የአርሶ አደሮችን የበረታ ክንድ ድህነትን አሽቀንጥሮ ለመጣል ይረዳል ብለዋል።
በባሶ ሊበን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ አትክልት እና ፍራፍሬ ቡድን መሪ ሀይሉ ልመንህ በወረዳው 1 ሺህ 540 ሄክታር መሬት በዘር ይሸፈናል ብለዋል። እስካሁንም 1 ሺህ 242 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። በሥራው ላይ 4 ሺህ 110 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል። 3 ባለሀብቶችና 139 ወጣቶችም መሬት ወስደው እየሠሩ ነው ብለዋል። ከ440 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ከኤጅ ጂ ፒ የቀረበ ሲኾን ቀሪውን 69 ኩንታል አርሶ አደሮቹ የራሳቸውን ዘር እንዲጠቀሙ ተደርጓል ነው ያሉት።
በወረዳው የሚገኙትን ሦስት ወንዞችን በተለያየ ቦታ በመገደብ አርሶ አደሮች የውኃ እጥረት እንዳይገጥማቸው እየተሠራ ነው። 63 ሺህ 900 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎም ታቅዷል። ባለፈው ዓመትም 583 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት በመገኘቱ ለአርሶ አደሮች መነሳሳትን ፈጥሯል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ ተሻለ አይናለም በ2015 ዓ.ም 250 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ይሸፍናል ብለዋል። ባለሙያው እንዳብራሩት፡-
• 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ ታቅዷል።
• 500 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ 375 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለመጠቀም ታቅዷል።
• በሥራው ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ በእቅድ ተይዟል።
እስካሁን በአፈጻጸም ደረጃ:-
• እስካሁን 200 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሷል።
• 112 ሺህ 603 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል።
• 189 ሺህ 600 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቧል።
• 482 ሺህ 831 ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቧል።
• 157ሺህ 880 ኩንታል ማዳበሪያ፣168 ሺህ 904 ነጥብ 5 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል።
• 442 ሺህ 473 አርሶ አደሮች በሥራው ላይ ተሳትፈዋል።
• በዘር ከተሸፈነው 112 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 2 ሺህ 404 ሄክታር መሬት በዩኒቨርሲቲዎች፣ 3 ሺህ 344 ሄክታር መሬታ በባለሀብቶች የተዘራ ነው።
• ሥራውን ወደ ዘመናዊነት ለማምጣት ከ14 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በትራክተር እንደታረሰ ታውቋል።
• ዩኒቨርሲቲዎች አርሶ አደሮችን በአሠራር፣ በግብዓትና በቴክኖሎጅ እየደገፉ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በ2014 ዓ.ም ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኩር ጋዜጣ – ታኅሣሥ 24/2015 ዓ.ም ዕትም
Next articleምድር የሰጠችን እምቅ ሃብት! – ማዕድን