
ወልድያ: ታኅሣሥ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፒፕል ቱ ፒፕል ዩ ኤስ ኤ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከድርጅቱና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በካናዳ ከሚገኘው ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በሀብሩ ወረዳ ውርጌሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስር የመማሪያ ክፍሎችን ገንብተው አስረክበዋል፡፡
ፒፕል ቱ ፒፕል ዩ ኤስ ኤ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ዳንኤል አውራሪስ ፕሮጀክቱ በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው ሀብሩ ወረዳ ውርጌሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ቤተ መጻሕፍት የማሟላትና ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በመልሶ ግንባታው ከ2ሚሊየን ብር በላይ ወጭ መደረጉን አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
አስተዳደር ምክር ቤቱን በመወከል በርክክቡ ወቅት የተገኙት ሀያት ኀይሌ በወረዳው ከ96 በላይ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡ ጉዳት የደረሰበትን የውርጌሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መልሶ በመገንባት የዜግነት ድርሻቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት የበላይ ጠባቂ እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የክብር ዶክተር ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ በማሰብ ለተከናወነው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ቤተክርስቲያኗ ከልማት ድርጅቶች ጋር በመሆን ለትውልድ ግንባታ የምታደርገውን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል የገለጹት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸው ስለሆነ መላ ኢትዮጵያዊያን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ:–ባለ ዓለምየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!