
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች፣ የእንስሳት ስርቆትና ሕገወጥ የሰው ዝውውርን ለማስቆም የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የሱዳን የአንኩራና የከርቸዲ የጸጥታ መዋቅር፣ የቀበሌ አሥተዳደሮች፣ የመከላከያ መሪዎች፣ የቋራ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የወረዳው የጸጥታ ኀላፊ፣ የጸጥታ መዋቅሮች፣ የነብስ ገቢያ ቁጥር 4 የቀበሌ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ውይይቱ ተካሂዷል።
በሕዝብ ለሕዝብ ውይይቱ የተገኙት የቋራ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ደሳለኝ ሞገስ በመድረኩ በኢትያጵያና በሱዳን በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች፣ የእንስሳት ስርቆትን በተመለከተ፣ ሕገወጥ የሰው ዝውውርን ለማስቆም ትኩረት ያደርገ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።
ከአሁን በፊት ተደጋጋሚ ውይይቶች የተደረገ መኾኑን የገለፁት አቶ ደሳለኝ በውይይቶች ሲፈጠሩ የነበሩ የእንስሳት ስርቆትን በሁለቱም ሀገራት በኩል እንዲመለስ ማድረግ የተቻለ መኾኑን አንስተዋል።
ውይይቱን በቀጣይነት በማጠናከር ከእንስሳት ስርቆቱ በተጨማሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስቆም በሁለቱ ሀገራት ሰላማዊ ግንኙነት ለመፈጠር መሠራት እንዳለበት ተመላክቷል።
የቋራ ወረዳ የሰለምና ደኅንነት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ አስማረ፤ በሱዳንና በአጎራባች የቋራ ወረዳ ቀጣናዊ ትስስርን ሰለማዊ ለማድረግና በሁለቱም ሀገራት የመልካም አሥተዳደር ችግርን ማምጣት የሚችሉ ተግባራትን በዘላቂነት ለማስቆም መድረክ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
መድረኩ ከዚህ በፊት ሲደረጉ በነበሩ መድረኮች በርካታ ችግሮችን መፍታት የቻልንባቸው መድረኮችን ሲፈጥሩ እንደነበር የገለፁት አቶ አስማረ፤ በቀጠይም በቀጣናው ለመልካም አሥተዳድር ችግር የሚኾኑ የእንስሳት ስርቆትና የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም በሁለቱም ሀገራት በኩል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አንስተዋል።
በተለይ በሁለቱም በኩል የሚመለከታቸውን የበላይ መሪዎች ጋር የጋራ በማድረግ ለዘላቂ ሰላማዊ ግንኙነት ፈር የሚቀድ መኾኑም ተነግረዋል።
የሱደን መሪዎች በበኩላቸው በቀጣይ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ገልጸዋል። መረጃው የቋራ ኮሙኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!