በአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች ሰሞኑን የሚስተዋለው ቅዝቃዜ እስከ ጥር መጨረሻ ሊቀጥል እንደሚችል ተጠቆመ

132

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአንዳንድ ከፍተኛ የአገሪቱ ሥፍራዎች የሚስተዋለው ቅዝቃዜ እስከ ጥር መጨረሻ ሊቀጥል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የምርምር ክፍል ዴስክ ኃላፊ ሙሉዓለም አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከመደበኛው ለየት ያለ ቅዝቃዜ እየተስተዋለ ነው።

ቅዝቃዜው አዲስ አበባን ጨምሮ ከባህር ጠለል በላይ ከ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ሥፍራዎች ላይ የሚስተዋል መሆኑን ገልጸው እነዚህ ሥፍራዎች የሌሊትና ማለዳ እንዲሁም የምሽት ቅዝቃዜ ተስተውሎባቸዋል ብለዋል።

አሁን ላይ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ፣ በደብረ ብርሃን፣ በሃሮማያ፣ በደቡብ ከፍተኛ ሥፍራዎች እንዲሁም በመካከለኛውና ሰሜን ምስራቅ የሚገኙ ከፍተኛ ሥፍራዎች ላይ ቅዝቃዜው በርትቷል ነው ያሉት።

ለቅዝቃዜው ዋነኛ መነሻው ከምስራቅ አውሮፓ ተነስቶ የአረቡን መሬት አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ቀዝቃዛና ደረቅ አየር መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ቅዝቃዜ ለቀጣይ አንድ ወራት በመካከለኛው፣ በምስራቅና በደቡብ የአገሪቱ ከፍተኛ ሥፍራዎች ላይ እንደሚቀጥልና የመጠናከር ባህሪ ሊኖረው እንደሚችልም የአየር ትንበያ ጠቅሰው አስረድተዋል።

ኅብረተሰቡም ቅዝቃዜውን ከግምት በማስገባት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አሳስቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሌብነት ወንጀልን ለሚጠቁሙ ሰዎች ሕጉ ምን ዓይነት ከለላ ይሰጣል?
Next article” የፋሲል ጥበባት፣ የባሕረ ጥምቀቱ ምስጢራት”