የሌብነት ወንጀልን ለሚጠቁሙ ሰዎች ሕጉ ምን ዓይነት ከለላ ይሰጣል?

186

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት “ሙስናን መከላከል በተግባር” በሚል መሪ መልእክት ሀገራዊ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህ ሌብነትን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የኅብረተሰቡ ሚና የጎላ ነው።

ይኹን እንጂ አንድ ግለሰብ፤ ቡድንን አለያም ግለሰብን በሌብነት ወንጀል በሚያጋልጥበት ወቅት ሕጉ ምን ዓይነት ከለላ ያደርግለታል ስንል በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ምናለ አሞኘን አነጋግረናል።

ባለሙያው ሙስናን ለመከታተልና ለመመርመር የጠቋሚዎችና ምስክሮች መኖር አስፈላጊ ነው ብለዋል። “ጥቆማ ማቅረብ መብት ነው” ያሉት የሕግ ባለሙያው የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎች ላይ ግን ጥቆማ ማድረግ ግዴታ እንደኾነ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 11 ላይ በግልጽ የተደነገገ እንደኾነ አስረድተዋል።

የሙስና ወንጀል የሀገርን ኢኮኖሚ አደጋ ላይ ስለሚጥል ወንጀሉን ለመከላከል የአንድ ተቋም ትግል ብቻ ሳይኾን የሕዝብ ትግል ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል።

የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመግታት ጠቋሚዎችና ምስክሮች ማንነታቸውን ገልጸው ወይም ደብቀው የሚሰጡት ጥቆማ መኖሩን ገልጸዋል። የሚሰጡት ጥቆማ፦

👉ወንጀሉ በማን እንደተፈጸመ
👉ወንጀሉ መቼ እንደተፈጸመ
👉ምን ወንጀል እንደተፈጸመ
👉ወንጀሉ ለምን እንደተፈጸመ
👉የት ቦታ እንደተፈጸመ እና
👉እንዴት እንደተፈጸመ
ጥቆማ ተቀባዩ ከጠቋሚዎች ዝርዝር መረጃ እንደሚሰበሰብ አቶ ምናለ አስረድተዋል።
ጥቆማ፦
👉በአካል
👉በስልክ
👉በፋክስ
👉በቴሌግራም
👉 በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እና በመሳሰሉት መንገዶች ሊቀርብ እንደሚችልም አብራርተዋል። ጠቋሚዎቹ ከላይ የተጠቀሱትን ዝርዝር መረጃዎችን ለማቅረብ እንደማይገደዱ ያነሱት የሕግ ባለሙያው የሙስና ወንጀል መርማሪው በተሰጠዉ መረጃ ላይ በመመስረት ሙሉ መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ ማከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የለሙስና ወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮችን ከጥቃት ለመከላከል የጸረ ሙስና ልዩ የሥነሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 እና የምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ከለላ እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

ለሙስና ወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች ከሚሰጡ ከለላዎች ውስጥ የሥራ ቦታን መለወጥ፣ የዓይን ቁራኛ ጥበቃ ማድረግና የራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ መስጠት በአዋጆቹ የተፈቀደ እንደኾነ የሕግ ባለሙያው ገልጸዋል። ይኹን እንጂ የጥቆማ አቀባበል ሂደቱ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊኾን እንደሚገባ ባለሙያው መክረዋል። ጠቋሚዎች ጥቆማ የሚያቀርቡበትን ምክንያት መመርመር እንደሚገባም ነው የመከሩት። “አንዳንድ ጠቋሚዎች ጥቅም ለማግኘት ፣ሹመትና ጥቅማጥቅም ለማግኘት ፣በቂም በቀል እንዲኹም የወንጀል ተሳታፊ መኾናቸውን ለመደበቅ ጥቆማ ሊያቀርቡ ስለሚችሉ ጥቆማ ተቀባዩ ጥቆማ ሰጭዎችን በጥንቃቄ ማየትና መመርመር ይገባዋል” ብለዋል።

ጥቆማ አቅራቢዎች “የጠቆምኩት ጥቆማ የት ደረሰ?” ብለው የመጠየቅ መብት እንዳላቸው አስረድተዋል። የሚቀርቡ ጥቆማዎች ምላሽ የሚሰጥባቸው ቅደም ተከተል እንዳላቸውም ተናግረዋል። በመሆኑም ሕጉ ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን ከለላ መሠረት በማድረግ የሀገርን ሐብት የሚመዘብሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በማጋለጥ እና በመጠቆም ማህበረሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቶ ምናለ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥምቀቱ አድማቂዎች!
Next articleበአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች ሰሞኑን የሚስተዋለው ቅዝቃዜ እስከ ጥር መጨረሻ ሊቀጥል እንደሚችል ተጠቆመ