
ጎንደር: ታኅሣሥ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አበው በምስጋና ይከቧታል፣ ያለ ማቋረጥ ይጸልዩባታል፣ ለምድር በረከትና ረድኤት ይኾን ዘንድ ይማፀኑባታል። አምላክ ምድርን በቸርነቱ እንዲጠብቃት፣ በደሏን እና ክፋቷን ይቅር እንዲላት፣ እንደበደሏ ሳይኾን እንደቸርነቱ እንዲያያት፣ በፅናት ይተጉባታል። በዚያች ሥፍራ ስጋ እየደከመች፣ ነብስ እየበረታች ታድራለች፣ በዚያች ሥፍራ ረድኤት ይዘንባል፣ ቅዱስ መንፈስ፣ ከቅዱሳኑ ጋር ይኖራል። በዚያች ሥፍራ የነብስ ጥጋብ እንጂ የሰጋ ጥጋብ አይታወቅም፣ አበው ስጋቸውን ጎድተው ነብሳቸውን ክሰው ይኖራሉ።
ለምስጋና ይሰባሰቡባታል፣ ለጸሎት እና ለምሕላ ይጠራሩባታል፣ ለበረከት ይጓዙባታል፣ ለፅድቅ ይጸልዩባታል። በየባዕታቸው ኾነው ለጌታ የተገባችውን ምስጋና ያቀርባሉ፣ በሰርክ ይማፀናሉ፣ ጌታም በረከትና ረድኤት ይሰጣቸዋል፣ የልባቸውን መሻት ይፈፅምላቸዋል፣ ምድርን ይባርክላቸዋል።
ሊቃውንቱ በተቀደሰው ሥፍራ ውስጥ ኾነው ያመሰግናሉ፣ ረጃጅም ዛፎች በቀስታ ሲያረግዱ እነርሱም ለፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡ ይመስላሉ፣ ምስጢራዊው ሕይቅ ይከባታል፣ በማዕበል እየተወዛወዘ ምስጋና የሚያቀርብ ይመስላል። ትናንት በነበረችበት መጎናፀፊያ ዛሬም አለች፣ ትናንት በነበረችበት ክዳን ዛሬም ቀጥላለች። ትናንት ከነበረችበት መጎናጸፊያ ውጭ ሌላውን በላይዋ ላይ አትደርብም፣ የዛሬው መጎናፀፊያ ለእርሷ አልተገባም፣ ሊያስውባት፣ ሊያሳምራት፣ እና ሊያስጌጣት አይቻለውም።
እርሷን የሚያስውባት፣ እርሷን የሚያሳምራት አስቀድማ የለበሰችው፣ ለብሳውም የኖረችው፣ አሁንም ለብሳው ያለችው፣ ወደ ፊትም ለብሳውም የምትኖረው ነው። ለእርሷ የተገባው የጥንት የጠዋቱ መጎናፀፊያ ነው። እርሷ የለበሰችውን ብዙዎች ንቀውታል፣ በዘመኑ መጎናፀፊያ ቀይረውታል፣ እርሷ ግን ዛሬም እንዳማረችበት አለች። ነገሥታቱ ከፈረሶቻቸው እየወረዱ እጅ ነስተውባታል፣ ጎራዴያቸውን ከሰገባው እየመዘዙ፣ የራስ ዘወዳቸውን እያወለቁ ሰግደውባታል፣ ዘመናቸው የተባረከ ይኾን ዘንድ ተማፅነውባታል፣ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ በአፀዷ ሥር በግንባራቸው እየተደፉ ጸሎት አድርሰውባታል፣ በሀገርና በሕዝብ ሰላም ይኾን ዘንድ ፈጣሪያቸውን አብዝተው ለምነውባታል።
ብዙዎች ከእርሷ አፀድ ሥር ለመጸለል ገስግሰዋል፣ በአፀዷ ሥርም ተፀልለው ኖረዋል። ነብሳቸውን አበርትተው፣ ስጋቸውን አድክመው ተቀምጠዋል። በምስጢር ከተመላው፣ በምስጢርም ከሚኖረው፣ በምስጢርም ከፀናው ሐይቅ ዳርቻ ትገኛለች። ወለል ካለው የደምቢያ ምድር፣ ከጣና ሐይቅ ዳር፣ በክብርና በሞገስ፣ ከእነ ጥንት ውበቷ የምትኖር ገዳም ናት። ደብረ ሲና ማርያም ገዳም። በዘመነ አምደጽዮን እንደተሠራች ይነገርላታል። ታላቁ ንጉሥ አምደጽዮን በዘመናቸው አያሌ አብያተክርስቲያናትን አሰርተዋል፣ አያሌ ገደማትን አስገድመዋል። በእርሳቸው ዘመን ከተሠሩት ጥንታዊ ገዳማት መካከል የሐይቅ ዳሯ እመቤት፣ የእሳር ጎጆዋ ንግሥት፣ የጎርጎረዋ ልእልት ደብረ ሲና ማርያም ናት።
ደብረ ሲና ማርያም እጅግ የረቀቁ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሃብቶችን የያዘች፣ ዘመናትን በተሻገሩ ስእላት የተዋበች፣ ከሰባት መቶ ዓመታት በላይ በእሳር ክዳን የኖረች ገዳም ናት። ከሳር ክዳን ውጭ ከእርሷ ጣሪያ ላይ ተሰቅሎ መቆዬት የሚቻለው ዘመን አመጣሽ ክዳን የለም። አበው ዘመን አመጣሹ ክዳን ከእርሷ ጣሪያ ላይ በተሰቀለ ጊዜ በኀይሏ አንስታ ትጥለዋለች፣ ከእርሷም ታርቀዋለች ይላሉ። ከጥንት እስከዛሬ ድረስ በእሳር ክዳን አምራና ተውባ ትኖራለች እንጂ። ወደፊትም ከእሳር ክዳን ውጭ ሌላው ለእርሷ የተገባ አይደለም ይሏታል።
የደብረ ሲና ማርያም እና በዙሪያዋ ያሉ ገደማት፣ አድባራትና እና ታሪካዊ ሥፍራዎች አስጎብኚ አንድሪያኖ ተሰማ በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ከሸዋ ደብረ ሲና በመጡ አባ ኤስድሮስ በተባሉ አባት የተሠራች እንደኾነች ነገሮናል። ሙሴ ፅላት የተቀበለባት የሲና ተራራ፣ አባ ኤስድሮስ የመጡባት ደብረ ሲና እና ቅድስት ማርያም ገዳም የተገደመችባት የጎርጎረዋ ደብረ ሲና እነዚህ ሦስት ሥፍራዎች ስም ያገናኛቸው፣ የየራሳቸው ከፍ ያለ ታሪክ ያላቸው ሥፍራዎች ናቸው። ደብረ ሲና ማርያምን አባ ኤስድሮስ በተወለዱባት ሥፍራ ሥም እንደሰየሟት ይነገራል።
703 ዓመታት እድሜ ያላት ደብረ ሲና ማርያም በረቀቀ ጥበብ የተሠራች፣ የትናንቱን ጥበብ እየገለጠች ያለች ገዳም ናት። የከበቧት ጥንታዊ ዛፎች እያረገዱ ከውበት ላይ ውበት ይሰጧታል። አእዋፋት በሕብረ ዝማሬ ያደምቋታል፣ የጣና ማዕበል ያጅባታል። በእርሷ አፀድ ሥር የደረሰ ሁሉ ልቡ በሀሴት ትፈነድቃለች፣ ነብሱ መልካሙን ማዕዛ ታሸትታለች፣ ጀሮው መልኳሙን ነገር ትሰማለች፣ ዓይኑ የተዋበውን ታያለች፣ እጁ የረቀቀውን ትዳስሰዋለች፣ እግሩ በተባረከው አፀድ ሥር ትረማመዳለች። ዙሪያ ገባዋን እየተመለተ የማይደነቅ፣ ስለ አሰራሯ ጥበብ፣ ስለ ታሪኳም ርዝማኔ የማያደንቅ የለም።
በአፀዷ ግርጌ ለምስጋና የበረቱ አበው አይታጡባትም፣ መቁጠሪያቸውን ይዘው ሳይሰለቹ ይማፀናሉ፣ አንደበታቸው ለምስጋና ብቻ የምትከፈት፣ ዓይኖቻቸው ወደ መልካሙ ነገር ብቻ የሚመለከቱ የተቀደሱ፣ የተባረኩና የተመረጡ አበው መነኮሳት አይጠፉባትም። በአፀዷ ሥር ሰላም፣ ደስታ፣ ፍቅር፣ በረከትና ረድኤት ሞልቷል። በበረከቷና በረድኤቷ የሚኖሩት የብዙ ብዙ ናቸው።
በዚያች ያማረችና የተዋበች ገዳም ውስጥ እቴጌ መለኮታዊት ስእል አስለውባታል፣ ነገሥታቱ በትህትና ዝቅ እያሉ ሥጦታ አበርክተውባታል፣ መልካሙን ነገርም አድርገውባታል። አባ ኤስድሮስ በጣና ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ለአካባቢው ባላባቶች ምን ባደርግላችሁ ትወዳላችሁ ብለው ጠየቋቸው፣ እነርሱም ገዳም ይገድሙልን፣ በገዳሙም ለፈጣሪያችን ምስጋና እያቀረብን፣ ኪዳን እያደረስን፣ ቅዳሴ እያስቀደስን፣ ስጋውና ደሙን እየተቀበልን እንኖራለን አሏቸው። እርሳቸውም የጠየቋቸውን ይፈፅሙ ዘንድ ፈጣሪያቸው ይረዳቸው ዘንድ በጸሎት በረቱ። ደብረ ሲናና ማርያምንም አሰርተው ገዳም ገደሙ። በዚያች የተቀደሰች ሥፍራም ሕዝብ ሁሉ ተሰባሰበባት፣ ለፈጣሪው ምስጋና አቀረበባት፣ የምስጋናውንም ፍሬ ተቀበለባት። መልካሙን እና የማያረጀውን ካባ ለበሰባት።
ደብረ ሲና ማርያም ከጉላላቷ ላይ ሰባት የሰጎን እንቁላሎች አሉባት። እነዚህ የሰጎን እንቁላሎች ዝም ብለው የተሰቀሉ አይደሉም። ምስጢርን እንዲገልጡ በምስጢር ተሰቀሉ እንጂ። አበው በቅድስና ጠበቋት፣ ወደ ፈጣሪያቸው ምስጋና እና ምልጃ እያቀረቡ አክብረው አስከበሯት። ዘመናትንም ከእነ ግርማዋ አቆዪዋት። ምዕራፈ ቅዱሳን ጽዮን ደብረ ሲና ማርያም እየተባለች ትጠራለች። እርሷን የሚያከብራትን በበረከት ትመለዋለች፣ በክፋት ተነሳስቶ የሚነካትንም ትቀጠዋለች፣ እርሷን ማክበር እንጂ መድፈር የሚቻለው የለም። በተለያየ ዘመን ገዳሟን ሊያፈራርሱ የመጡ ጠላቶችን ንቦች እንዳባረሯቸው፣ በመንፈስ ቅዱስ እየታዘዙ ገዳሟን የሚጠብቁ ንቦች ዛሬም ከእርሷ አጠገብ እንደሚኖሩ አንድሪያኖ ነግሮናል።
ዘመናትን የተሻገሩ የረቀቁ በሮች እና መስኮቶች አሏት፣ ቅኔ ማሕሌቱ፣ ቅድስቱና መቅደሱ በጥበብ የተሠሩ ናቸው። ምዕራፈ ቅዱሳን ጽዮን ደብረ ሲና ማርያም ገዳም በዓመታት ልዩነት ከሚቀዬረው የእሳር ክዳን ውጭ የታደሰ ነገር የላትም። ሁሉም ጥንት አጊጠው እንደተሠሩ ዛሬም አጊጠው ይኖራሉ። በውጭ በኩል ሃያ አራት መሰሶዎች አሏት፣ እነርሱም ሃያአራቱን ካህናተ ሰማያት ይወክላሉ። በውስጥም አሥራ ሁለት አሉ። እነርሱም የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ተምሳሌት ናቸው። አባ ኤስድሮስ ገዳሟን ባሰሩ ጊዜ አሥራ አንድ መሰሶዎችን ገዙ፣ መግዛት የሚፈልጉትም አሥራ ሁለት ነበር። ለአንደኛው ግን መግዣ ገንዘብ አነሳቸው። እርሳቸውም አሥራ አንዱን ብቻ ገዝተው ተመለሱ። ገዳሟ በተሠራችበት ሥፍራ በደረሱ ጊዜ ገንዘብ አንሷቸው ጥለውት የመጡት መሰሶ በመንፈስ ቅዱስ መጥቶ ደርሶ አገኙት። ያም መሰሶ ገዳሟን ካሳመሯት አሥራ ሁለት መሰሶዎች መካከል አንደኛው ኾኖ ዛሬ ድረስ እንዳለ አስጎብኚው ነግሮናል።
ጣና እንደ አገልጋይ ይታዘዝላታል፣ ለዘመናትም ያገለግላታል፣ በእርሷ አጸድ ሥር እልፍ አእላፍ ምስጢራት ሞልተዋል። ባዩዋት ቁጥር አዲስ ናት። ታይታ አትጠገብም፣ ተመርምራም አይደረስባትም፣ እፁብ ድንቅ ናትና። እርጋታ ባለበት በረከት በሚበዛበት አፀዷ ሥር የተገኘ ሁሉ መልካሙን ነገር ሁሉ ያያል። በአየውም ነገር ደስ ይሰኛል። ምዕራፈ ቅዱሳን ጽዮን ድበረ ሲና ማርያም ገዳም በገዳማዊ ሥርዓት ትተዳደራለች። መነኮሳት እና ዲያቆናት ያገለግሏታል፣ ኪዳን ያደርሱባታል፣ ቅዳሴ ይቀድሱባታል። የሐይቅ ዳሯ እመቤት፣ የእሳር ጎጆዋ ንግሥት የትናንቱ ጥበብ ከእነ ሙሉ ውበቱ የሚታይባት፣ ሃይማኖት የፀናባት፣ ታሪክ የመላባት፣ ምስጢራት የሚከቧት፣ ከከበሩት የከበረች፣ ከተመረጡት የተመረጠች፣ ከተቀደሱት የተቀደሰች ውብ ገዳም ናት። ይሂዱባት እየተመለከቱ ውበትን ያደንቁባት፣ መልካም ሥርዓትን ይማሩባት፣ በረከትን ይቀበሉባት።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck