
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሥራ አጥነት የመንግሥት ትልቁ ፈተና እየኾነ ከመጣ ውሎ አድሯ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃ እንሚያመላክተው በየዓመቱ 2 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎች ይፈጠራሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ በየዓመቱ 3 ሚሊዮን አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር አቅጀ እየሠራሁ ነው ይላል።
ችግሩ ግን የሥራ አጡን ቁጥር መግታት አልተቻለም፡፡ በመንግሥት መሥሪያቤቶች በቅጥር የሚፈጠረው የሥራ እድል አንዱ የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነሻ ዘርፍ ነው፡፡
ኾኖም ግን የሥራ እድሉ የሥራ ፈላጊውን ቁጥር የሚመጥን አለመኾኑ ብቻም ሳይኾን ለብልሹ አሠራር መጋለጡ ደግሞ ሌላው ፈተና ኾኗል፡፡
በተቋማት ከሥራ ቅጥር እስከ ደረጃ እድገት እና ዝውውር የሰው ሃብት አስተዳደር አጠቃላይ ስምሪቱን የሚመራው በየደረጃው ባለው የሲቪል ሰርቪስና ሰውሃብት ልማት ኮሚሽን ነው፡፡
ዘርፉ በተሰጠው ኃላፊነት ልክ እየሠራ አይደለም ከሥራ ቅጥር እስከ ደረጃ እድገት እና ዝውውር አጠቃላይ ስምሪቱ የሰው ሃብት አስተዳደር ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ ነው የሚሉ ቅሬታዎችን የሚያስተናግድ ዘርፍ ኾኗል፡፡
ቅጥር በዘመድ ነው፣ ቅጥር በገንዘብ እየተገዛ ነው፣ ለመቀጠር ተፈላጊው እውቀትና ሙያ ሳይኾን ገንዘብ መክፈል ኾኗል፣ የደረጃ እድገትም ዝውውርም በወዳጅ ዘመድ እና በጥቅም ትስስር ኾኗል የብዙዎች አቤቱታ እየኾነ በሕግ አምላክ ብሎ ሕግ የሚዳኘው አልኾነም እየተባለ ነው፡፡
በመንግሥት ተቋማት እውቀቱና ሙያው ያለው፣ ለሙያው የሚመጥን ሰው ሁሉ መብቱን እና እድሉን ተጠቅሞ ተቀጥሮ መሥራት እየተፈተነ በብልሹ አሠራር እየተጠለፈ ውስብስብ ሂደትን ወልዷል ነው የሚባለው፡፡
ለመኾኑ ይሄ አቤቱታ ዘርፉን ለሚመራው ተቋም ጀሮ እየደረሰ ይኾን፣ ከኾነስ ችግሮችን ለይቶ ከመከላከልና እርምጃ ከመውስድ አንጻር ምን እየተሠራ ነው የሚለውን ጉዳይ ማንሳት ተገቢ ይኾናል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አሚኮ ኦንላይን ሚዲያ የክልሉን ሲቪል ሰርቪስ እና ሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ካሳ አበባውን ጠይቋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሯ ይናገራሉ ችግሩን ወቀሳውን እናውቀዋለን ግን ከአሉቧልታ የዘለለ ተጨባጭ ማስረጃ እየጠፋ፣ አለ የሚባለውን ችግር አግኝቶ እልባት ማስቀመጥ ፈተና ኾኗል ይላሉ፡፡
እርግጥ ነው ቅጥር በገንዘብ እየተገዛ ነው የሚል አቤቱታ ይሰማል፣ ከደረጃ እድገት እስከ ዝውውር ጭምር በጥቅምም ትስስር እየተፈጸመ ነው የሚለው ብዙ ነው፡፡ በየደረጃው ጥቆማዎችም ለኮሚሺኑ ይደርሳሉ የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሯ ጥቆማዎችንም ኾነ አሠራሮችን ስንፈትሽ ግን በሚባለው ልክ የተፈጸመን ብልሹ አሠራር ማግኘት አልተቻለም ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ በየደረጃው ለሚነሱ ቅሬታዎች ችግሩን ለማግኘት እና ለመከላከልም ኾነ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ይላሉ ኮሚሽነሯ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ከክልል እስከ ታችኛው ቀበሌ የደረሰ በ2014 ዓ.ም የንቅናቄ መድረክ ተካሂዶ ነበር ይላሉ፡፡
መድረኩ በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እየተመራ የተቋማት መሪዎችም ፈጻሚዎች ባሉበት በተደረገ ውይይት የተደረሰበት ነገር የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር አለ የሚል ነው ብለዋል፡፡
የሚባለው የሚወራው ሁሉ እውነት ነውም ስህተት ነው ማለት አይቻልም የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሯ ይኽን አለ የሚባለውን ብልሹ አሠራር ለመከላከል እና እርምጃም ለመውሰድ ችግር አለ ከሚል የዘለለ መረጃና ማስረጃ የሚሰጥ ሰው ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡
ታዲያ በዘርፉ አለ የሚባለውን ሙስናና ብልሹ አሠራርን በልኩ መከላከል ያልተቻለው ”አሠራሩን የቀደሙ ሌቦች”ተፈጥረው ይኾን የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ምክትል ኮምሽነሯ ካሳ አበባው በሙስናና ብልሹ አሠራር ሰጭም ተቀባይም በድብቅ የሚፈጽሙት በመኾኑ ነገሩን ውስብስብ አድርጎታል ባይናቸው፡፡
ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት፣ ተገቢ ያልኾነ የጥቅም ትስስር በመፍጠር በብልሹ አሠራርና ሙስና ተጠልፎ ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት የሥነ-ምግባር ዝቅጠት ነው ይሉታል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሯ እንደተናገሩት አሁን ላይ ብልሹ አሠራርንና ሙስናን ለመዋጋት በፍትሕ፣ ፀረ-ሙስናና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የጋራ ግብረኀል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
ለዚህም ተጨባጭ ጥቆማና ማስረጃ በመስጠት በኩል ሁሉም ሰው ለሕግና ሥርዓት መረጋገጥ የኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!