
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ ከታኅሣሥ ጀምሮ የሚከናወኑ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክዋኔዎቹ ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ዓይነተኛ ሚናን እንደሚጫወቱ ቢሮው ጠቁሟል።
መግለጫዉን የሰጡት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሒር ሙሐመድ የልደት በዓል በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ቢከበርም በላሊበላ ከተማ በልዩ ሁኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውንና እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። በተለይ በጦርነቱና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጎድቶ የነበረውን ቱሪዝም ለማጠናከር የተሻለ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ነው አቶ ጣሒር የገለጹት።
በጎንደር ከተማ በተለየ መልኩ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል፣ በሰሜን ሸዋ የሚከበረው በኢራንቡቲ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል፣ በእንጅባራ ከተማ የሚከበረውን የአገው ፈረሰኞች በዓል፣ በደብረ ታቦር ከተማ የሚከበረውን የመርቆርዮስ በዓልና ሌሎችንም በዓላት በደመቀ መልኩ እንዲከበሩ ቢሮው ከአካባቢው አሥተዳደሮችና ማኅበረሰቡ ጋር እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በሰከላ ላይ ሚከበረውን የግዮን በዓል በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን የገለጹት ኀላፊው ለሁሉም በዓላት ለሚታደሙት እንግዶች የቱሪዝም ትውውቅ በማድረግ ዘርፉን የማጠናከር ሥራ እየሠሩ መኾኑን አመላክተዋል። አቶ ጣሒር እንዳሉት ቢሯቸው ከዓመት ወደ ዓመት የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር እየሠራ ነው።
በተለይ በዓላቱ በጎንደርና በላሊበላ ከተሞች ሲከበሩ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይኖር ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል። የዋጋ ንረቱ ቱሪስቶችን ሊጎዳ ስለሚችል አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምት የመውሰድ ተግባር እንደሚፈጸም አስገንዝበዋል።
ነጋዴዎች የበዓላቱን ድባብ ማጠልሸት እንደሌለባቸው ነው አቶ ጣሒር የጠየቁት። በጥር ወር ብቻ ሳይኾን ዓመቱን ሙሉ የሚመጡ እንግዶች በተለይ የአገልግሎት ዘርፉን ተጠቃሚ ስለሚያደርጉ አስተማማኝ ጸጥታ እንዲኖር፣ የዋጋ ማስተካከያ በማድረግ፣ የአካባቢን ጽዳት በመጠበቅ በኩል ተገቢው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን አስረድተዋል።
“አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግጁ መኾናቸውንና አሁን ላይ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን ለእንግዶቻችን መጠቆም እፈልጋለሁ” ብለዋል። ከአስጎብኚዎችና ከሆቴሎች ማኅበር ጋር በመነጋገር ጎብኚዎች በተሳካ መልኩ ጎብኝተው እንዲመለሱም ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ቢሮው በየዞኑ ሲያካሂድ የነበረውን የወይዘሪት አማራ የቁንጅና ውድድር ከጥምቀት በዓል በኋላ የፍጻሜው ውድድር በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።
በዞን ደረጃ የቁንጅና ውድድርን ያሸነፉ የቁንጅና ተወዳዳሪዎች በካምፕ ኾነው ተገቢውን ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋልም ብለዋል። የቁንጅና ተወዳዳሪዎቹ የቱሪዝም አምባሳደር ኾነው እንዲወጡ እየሰለጠኑ መኾኑን ነው አቶ ጣሒር የገለጹት።
ኀላፊው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከቁንጅና ውድድሩ መርኃ ግብር በአንድ ላይ የድንቅ ምድር እውቅናና ሽልማት ፕሮግራምም ይካሄዳል። ውድድሩ ዓመታዊ ኾኖ እንዲቀጥል ይደረጋልም ነው ያሉት። ሁሉም ኢትዮጵያዊም ኾነ የውጭ ዜጎች በአማራ ክልል የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት ላይ እንዲታደሙ ቢሮው ጥሪ አድርጓል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!