
ባሕርዳር : መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ግብ ያስቆጥርልሃል፤ ኳስን ይዞ መጫዎት ግን አይችልም ይሉታል፡፡ እርሱ ደግሞ የእኔ ሕልም ኳስን አምስት ጊዜ መንካት፤ አምስት ግቦችን ማስቆጠር ነው፡፡ ይህ ትልቁ ሕልሜ ነው ይላል ከወደ ኖርዌይ የመጣው ግብ አዳኝ ኤርሊን ብራውንት ሃላንድ፡፡
የዓለምን ቀልብ የሳበው አጥቂ በሜዳ ላይ ኳስና መረብን ማገኛኘት ቀላል መስሎለታል፡፡ በለጋ እድሜው በታላላቅ እግር ኳስ ክለቦች ዓይን የገባው ሃላንድ በኢትሃድ አስፈሪው አጥቂ ኾኗል፡፡
ከጀርመን ቦርሲያ ዶርትመንድ ሲግናል ኢዱና ፓርክ እንግሊዝ ማንችስተር ሲቲ ኢትሃድ የደረሰው ሃላንድ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታይቶ የማይታወቀውን ታሪክ ሊጽፍ ይችላል እየተባለ ነው፡፡ ግብ አዳኙ ሃላንድ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ግቦችን በማስቆጠር አዲስ ታሪክ እንደሚጽፍ ይጠበቃል፡፡
አስፈሪው አጥቂ ትናንት አመሻሽ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ማንችስተር ሲቲ በሜዳው የጀርመኑን አርቢ ላይፕዝሽን ባስተናገደበት ጨዋታ 5 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ከሜዳው ውጭ 1ለ1 በኾነ ውጤት ጨዋታውን ያጠናቀቀው ሲቲ በሜዳውና በደጋፊው ፊት በእንግዳው ክለብ ከግማሽ ደርዘን በላይ ግቦችን በማስቆጠር 7 ለ 0 አሸንፏል፡፡

በአንድ ጨዋታ አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ሃላንድ በእግር ኳስ ሰዎች አድናቆት እየጎረፈለት ነው፡፡
ሃላንድ አምስት ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ኤርሊንግ ሃላንድ ሰው አይደለም ብሎታል፡፡ ሃላንድ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ 30 ግቦች ላይ ቀድሞ የደረሰ በእደሜ ትንሹ እና ፈጣኑ ተጫዋች በመኾንም አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል፡፡
የ22 ዓመቱ አጥቂ በዚህ የውድድር ዘመን 39 ግቦችን በማስቆጠር በአንድ የውድድር ዘመን ከዚህ አኃዝ ላይ የደረሰ የመጀመሪያው የሲቲ ተጫዋች ሆኗልም ብሏል ቢቢሲ በዘገባው። በአውሮፓ ቻምዮንስ ሊግ ዓይን አፋር የኾነው ማንችስተር ሲቲ ፊታውራሪነት ዘንድሮ ምን ያሳይ ይኾን የሚለው ይጠበቃል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!