“በተያዘው በጀት ዓመት ለማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

196
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ “አሳታፊ የጤና አገልግሎት ለወረዳ ትራንስፎርሜሽን ተፈፃሚነት” በሚል መሪ ሀሳብ የጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ፣ የንቅናቄና የእውቅና መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) የእናቶችንና የሕፃናት ጤና እንዲሻሻል ተላላፊና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተሠራው ሥራ ለውጥ ማስመዝገቡን ተናግረዋል። ኀላፊው እንዳሉት የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ እንዲኾን ባለሙያዎችን የመመደብ፣ የማሰልጠን እና የሕክምና ግብዓቶች እንዲሟሉ በሠፊው ተሠርቷል።
በ2014 በጀት ዓመት በተሠራው የተቀናጀ ሥራ 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሕዝብ የጤና መድኅን አባል በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ዶክተር መልካሙ አስረድተዋል። ከኅብረተሰቡና ከመንግሥታዊ ተቋማት በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ኅብረተሰቡ ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን ኀላፊው ጠቁመዋል።
ዶክተር መልካሙ እንዳሉት የለጋሽ ሀገራት ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ የሀገር ውስጥ ሀብትና ገቢን ማሳደግ ወሳኝ ኾኗል። በተያዘው በጀት ዓመት ወጪያቸውን መሸፈን ላልቻሉ ወገኖች ትላልቅ ተቋማት የጤና ወጪያቸውን በማገዝ ተቋማቱም ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ይሰራል። ይኽን ለማሳካት የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ቤተሰብ ምስረታ አደረጃጀት ወጥነት ያለው አሠራር መዘርጋቱን አስገንዝበዋል።
ከማኅበረሰቡ የሚሰበሰበውን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ኦዲት እያደረጉ መምራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ኀላፊው እንዳሉት የመንግሥትና የግል ተቋማትን አጋርነት በማጠናከር የጤና መድኅን ተግባራትን በጋራ መሥራት ያስፈልጋል። አኹንም ቢኾን የጤና አገልግሎት አሰጣጡ አጥጋቢ አለመኾኑን የጠቆሙት ኀላፊው የአገልግሎት እርካታ ያገኘው የክልሉ ሕዝብ 64 በመቶ መኾኑን አብራርተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ሁሉንም የክልሉን ሕዝብ የጤና መድኀን አባል በማድረግ በ2030 ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባለሙያውና አመራሩ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ኀላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአዘዞ አርበኞች አደባባይ የመንገድ ፕሮጄክቶች በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾላቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
Next articleየኢትሃዱ ግብ አዳኝ