የአዘዞ አርበኞች አደባባይ የመንገድ ፕሮጄክቶች በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾላቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

251

ጎንደር: ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አምስት ያክል ከንቲባዎች የተቀያየሩበት፣ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ ያነሱበት መንገድ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ ዘግይቶ ዛሬም ድረስ በግንባታ ሂደት ነው። የበርካታ ጎብኚዎች መዳረሻ የኾነችው ጎንደር መንገዱ በቶሎ ተጠናቆ ለነዋሪዎቿም ለጎብኚዎቿም ምቹ ይኾናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። የመንገዱ ግንባታ ግን ከተባለለት ጊዜ ዘግይቷል። የመንገዱ መዘግየትም ለነዋሪዎቹ ሕይወት ፈታኝ ኾኖባቸዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ጥላዬ በሬ  የመንገዱ መዘግየት በሕይወታቸው ላይ ጫና እያሳደረ መኾኑን ተናግረዋል። በእድሜያቸው ገፋ ያሉ እናቶች እና አባቶች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉም ገልጸዋል። ድልድዮች እና ነባር መንገዶችን ቀድመው እያፈረሱ በፍጥነት ስለማይሠሯቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እየተቸገሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ከአንዳንድ አካባቢዎች ላይ  በጥልቀት የተቆፈረ በመኾኑ በእድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች ከቤት ለመቀመጥ መገደዳቸውንም ገልጸዋል።

መንገዶች ተቆፍረው ለረጅም ጊዜ ስለሚቆዩ መንቀሳቀስ እንደማያስችሉም ነው የገለጹት። በዓላት ሲደርሱ ሥራው የተፋጠነ ይመስላል በዓል ሲያልፍ ግን ሥራው ያቆማል ነው ያሉት። ወላዶችን ሀኪም ቤት ለማድረስ መቸገራቸውንም ተናግረዋል። መንገዱ ከሚገባው ጊዜ በላይ ጊዜ የወሰደ መኾኑንም ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የጎንደር ከተማ ነዋሪ  ቦሰና ተሾመ መንገዱ በመጓተቱ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል። በመንገዱ አቅራቢያ የሚኖሩ ሕፃናት እና እናቶች በአቧራ ምክንያት እየታመሙ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። በበዓላት አካባቢ የመንገድ ሥራው ፈጠን ያለ መስሎ ከበዓላት በኋላ እንደሚዘገይም ገልጸዋል።

የመንገዱ አለመጠናቀቅ ለማኅበራዊ ሕይወት ፈታኝ ነውም ብለዋል። መንገዱን የሚያሠሩና አካላት የእኔ ብለው እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ማኅበረሰቡ የመንገድ ችግር ስላለበት ለሥራው ተባባሪ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የመንገድ ፕሮጄክቱ አስተባባሪ ሰብሳቢ ዳንኤል ከበደ መንገዱ በ2010 ዓ.ም ተጀምሮ በነበረበት ችግር በመካከል ቆሞ እንደነበር አስታውሰዋል።

የካሳ ክፍያ በመጓተቱ መንገዱ በሚፈለገው ልክ ሳይሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል። የከተማዋ አስተዳደሩ ትኩረት ማነስ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለ ስልጣን ትኩረት ባለመስጠቱና ኮንትራክተሩ የእኔ ብሎ ባለመሰራቱ ለመንገዱ መጓተት ምክንያት መሆኑን ነው ያስታወሱት።

ከብዙ መዝግየት በኋላ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጎንደር ላይ ቢሮ በመክፈት መንገዱ በትኩረት እንዲሠራ የማድረግ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።  አሁን ላይ ከተማ አስተዳደሩ መንገዱን ከሦስተኛ ወገን ማፅዳቱንም ገልጸዋል። የቀሩት ጥቂት ሥራዎችም ለመንገዱ እንቅፋት እንደማይኾኑ ነው የተናገሩት።  ኮንትራክተሩ አሁን ላይ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ገብቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። አሁንም ለፕሮጄክቱ የሲምንቶ አቅርቦት ችግር መሆኑን ነው የተናገሩት። የመንገዱ መዘግየት በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የኢኮኖሚ ጫና ማሳደሩንም ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ለመንገዱ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። የጎንደር ሕዝብም ከመንገድ ፕሮጄክቱ ሠራተኞች ጋር በመተባበር ሥራውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባው አመላክተዋል። ሁሉም ለመንገድ ፕሮጄክቱ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት። ጎንደር የሚመጥናት መንገድ ሊኖራት ይገባልም ብለዋል።

የአዘዞ አርበኞች አደባባይ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዳዊት ፀጋዬ የመንገድ ፕሮጄክቱ ከተጀመረ አምስት  ዓመታት ኾኖታል ብለዋል። ለመንገዱ 8 መቶ 71 ሚሊዮን ገደማ ብር በጀት ተይዞለት እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ሥራ አስኪያጁ በመካከል ተጨማሪ ሥራዎች በመኖራቸው አንድ ቢሊዮን ብር መድረሱንም አስታውቀዋል። የመንገድ ፕሮጄክቱ በሁለት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞለት እንደነበር ነው የተናገሩት። የመንገድ ፕሮጄክቱን ከሦስተኛ ወገን ነፃ የማድረግ ከፍተኛ የኾነ ችግር ማጋጠሙና በሌሎች ችግሮች መንገድ ተቋራጩ ምንም አይነት ሥራ ሳይሠራ ለአንድ ዓመት ከሦስት ወራት መቀመጡንም አስታውሰዋል።

የመንገድ ተቋራጩ መንገዱ ነፃ ኾኖ የማይሰጠኝ ከኾነ ማሽኖቼን አውጥቼ ወደ ሌሎች ፕሮጄክቶች እሄዳለሁ ብሎ ማስወጣት ጀምሮ ነበርም ነው ያሉት።  ከዚያ በኋላ ችግሮቹ ተፈትተውለት ወደ ሥራ መግባቱን ነው የተናገሩት። መንገድ ፕሮጄክቱ የሁለት ዓመት ጊዜ ያለው ቢኾንም ሥራ የተጀመረው ሁለት ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው ብለዋል።  ከሁለት ዓመታት በኋላ ሲጀምርም በርካታ ፈታኝ ነገሮች እንደነበሩ ነው የተናገሩት።

መንገዱ  የተጨመሩ ሥራዎችን ጨምሮ አሁን ላይ 52 በመቶ መድረሱንም አስታውቀዋል። እስከ ሰኔ ሠላሳ ድረስ ቀሪ ሥራዎችን ጨርሰን ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል። 48 በመቶ የሚኾነውን ሥራ እስከ ሰኔ ሠላሳ የማጠናቀቅ ሙሉ እምነት አለን ነው ያሉት። መንገድ ፕሮጄክቱ የሲሚንቶ ችግር እንዳለበትም አስታውቀዋል። የመንገድ ፕሮጄክቱን ጊዜ ያራዘሙት ተቋራጩ የቆመባቸው ጊዜያት ናቸው ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ተቋራጩ ወደ ሙሉ አቅሚ ሢሠራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ያመጣልም ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ከነበረባት የዲፕሎማሲ ውጥረት ወደ ተረጋጋ መንገድ መምጣቷን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።
Next article“በተያዘው በጀት ዓመት ለማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ