
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እና የሚሲዎን መሪዎች ወደ ሀገራቸው ተጠርተው ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ የልህቀት አመራር አካዳሚ ሥልጠና ጀምረዋል።
ሥልጠናው በተለይ በጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ አጋጥሟት የነበረውን የዲፕሎማሲ መቀዛቀዝ እና ችግር ወደ ተስተካከለ አካሄድ ለማምጣት ያለመ ነው።
የአፍሪካ ልህቀት አመራር አካዳሚ ዳይሬክተር ምህረት ደበበ (ዶ•ር) ኢትዮጵያ ባለፈው ጊዜ አጋጥሟት የነበረውን የስም መጠልሸት እና መፋዘዝ በአጭር ጊዜ እንደምትቀይሩ አምናለሁ ነው ያሉት። ይህ ሥልጠና አዲስ የዲፕሎማሲ መንፈስ፣ ጉልበት እና አቅጣጫ ይዛችሁ የምትሔዱበት አንደኾነ አምናለሁ ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ያለፈው ሁለት ዓመት ለሀገራችን ፈታኝ እና የዘመቻ ወቅት ነበር። በሀገራችን በውስጥ እና በውጭ አጋጥሞን የነበረው ከባድ ችግር አሁን አቅጣጫ ይዞ የጋራ የተረጋጋ አቅጣጫ ወደምናስቀምጥበት ኹኔታ ላይ መጥተናል ብለዋል።
ያንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍፍ የማለዘብ እና የማስገንዘብ መንገድን ተከትለን የመጣብንን ጫና መቀልበስ ችለናል ብለዋል አቶ ደመቀ።
በውስጥም በውጭም በመተባበር ወደ ጥሩ ቁመና እና ስብራትን ወደ መጠገን አውድ መጥተናል። በባለፈው ጊዜ በዋሽንግተን፣ በብራስልስ፣ በጄኔቫ እና በአፍሪካ ኅብረት ሚናን ለመወጣት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትንቅንቅ ተደርጓል። በሌሎች የአውሮፓ እና የእስያ አህጉራት ከፍተኛ ትግል በመክፈላችሁ አምባሳደሮቻችን ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አጋጥሞ የነበረውን ጦርነት ለመፍታት የተደረገው የሰላም ሰምምት ትግባራ በፍጥነት እና በመልካም አቅጣጫ ቀጥሏል ብለዋል።
እንደሚኒስትሩ ገለጻ የዲፕሎማሲ መንገዳችን አሁን ወደተረጋጋጋ ሁኔታ ማምጣት የተቻለ ቢኾንም በሰብአዊ መብት በሕዳሴ ግድብ እና በአዲስ የአፍሪካዊ ሚናዎች ላይ አዳዲስ ጫናዎች እያቆጠቆጡ በመኾኑ እነዚህን የሚታገል አቅም ማምጣት አለብን ብለዋል።
ዘጋቢ:- አንዱአለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!