በምዕራብ ጎንደር ዞን ችግር ሲፈጥሩ የቆዩ ታጣቂ ኀይሎች እጃቸውን ለሕግ በመሥጠታቸው አንጻራዊ ሰላም መገኘቱን የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

309

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ታጣቂ ኀይሎች በሚሠሩት እኩይ ሥራ ሰዎች ይታገቱ፣ ይገደሉ፣ ይፈናቀሉ እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያመጡ ይጠየቁ እንደበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ ነዋሪ አቶ ወረቀት አያሌው፤ መንግሥት ለታጣቂ ኀይሎች በሰላም እጃቸውን እንዲሰሠጡ ያደረገው እንቅስቃሴ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑ በጫካ በነበረበት ወቅት ሰዎችን ያግት ነበር፣ ይዘርፍ ነበር፣ ይገድል ነበር፣ ያፈናቅል ነበር፣ ማሳ ያቃጥል ነበር እንዲሁም ለማስለቀቂያ ገንዘብ ይቀበል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ቡድኑ የዞኑን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲያውክ መቆየቱንም አቶ ወረቀት ተናግረዋል፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ትጥቅ መፍታቱ ለአካባቢው ነዋሪ በጥቂቱም ቢኾን ትንፋሽ ሠጥቷል ነው ያሉት፤ አሁንም ቢኾን ቀሪዎቹ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲመለሱ መንግሥት እያደረገ ያለው የሰላም ጥሪ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ታጣቂዎችም ከዘረፋ፣ ግድያ ማፈናቀል ወጥተው ወደቀደመ ኑሯቸው እንዲመለሱ እና በሀገራቸው ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የድርሻቸውን ቢዎጡ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ታጣቂ ኀይሎች እጃቸውን ለሕግ በመሥጠታቸው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን አቶ ወረቀት ተናግረዋል፡፡
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዝዋል ባዬ በበኩላቸው ታጣቂ ቡድኑ ትጥቅ ፈትቶ በሰላም መግባቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰርቶ ለመብላት ወጥቶ ለመግባት ያስችለዋል ብላል፡፡

ወይዘሮ ዝዋል በአካባቢው የተፈጸመው ግፍ ዘግናኝ እና ተወዳዳሪ የሌለው መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ደፍሮ የወጣው ብቻ ሳይኾን እዚህ ኾኖ መረጃ የሚያቀብለው ቁጥሩ ብዙ ነው፣ ብዙ ቀስቃሽ አለ፣ መንግሥት ታጣቂዎችን ብቻ ሳይኾን ቀስቃሾችንም ጨምሮ ማስቆም አለበት ነው ያሉት፡፡

አሁን የመጣው ሰላም በዘላቂነት እንዲቀጥል በጫካ ያሉት ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመጡበት መንገድ እየተመቻቸ ነው ብለዋል፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ደነቅ አበባው፤ አካባቢው በውስጥ እና በውጭ ኀይሎች ችግር ሲደርስበት መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተገድቦ መቀየቱንም አስረድተዋል፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ወደ ሰላም መመለሱ ለሴቶች እና ለሕፃናት ትልቅ ደስታ ይዞ መጥቷል ነው ያሉት፡፡

ታጣቂ ቡድኑ ወደ ሰላም መምጣቱ ማኅበረሰቡ በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት እና አካባቢውን እንዲያለማ ለማድረግም ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በአካባቢው ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች እና የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ በርካታ ሠራተኞች ወደ አካባቢው ይመጣሉ፤ ነገር ግን ታጣቂ ቡድኑ መኖሩ ለሥራም ኾነ ለእንቅስቃሴ ፈተና እንደነበር አስረድተዋል፡፡ መምሪያው ነዋሪዎች ያለ ሥጋት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ቀሪ የታጣቂው ቡድን አባላት ወደ ሰላም እንዲመለሱ አየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኑሯችንም ጣና ነው፣ የኑሮ መሠረታችንም አሳ ነው ” በአሳ ሃብት የተሰማሩ ወጣቶች
Next articleበኩር ጋዜጣ – ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም ዕትም