
ጎንደር: ታኅሣሥ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገሪቱ ግዙፉ ሐይቅ ጣና የበርካታ ዜጎች ጉሮሮ ነው። በዙሪያ ገባው የሠፈሩ ወገኖች ጣናን የሕይወታቸው መሠረት አድርገው ይኖራሉ። ጣና ሐይቅ ለብዙዎች የመኖር ምስጢር ነው። ጣና ለብዙዎች ልብስና ጉርሳቸው ነው።
በስፋት ከጣና ሐይቅ በሚዋሰነው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚኖሩ ነዋሪዎችም ሕይወታቸው ከጣና ሐይቅ ጋር የተሳሰረ ነው። አምስት ወረዳዎች በጣና ዳርቻዎች ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ካለው አቅም አንፃር በአሳ ሃብት ምርት ተጠቃሚ አይደለም። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከጎንደር ዞሪያ እስከ አለፋ ድረስ በጣና የሚከበብ ዞን ነው። ዞኑ ኑሯቸውን በጣና ዙሪያ ያደረጉ በርከታ ነዋሪዎች አሉት። ነገር ግን ጣና በስፋት እንደሚያዋስነው ዞን በአሳ ሃብት ምርት ተጠቃሚ አልኾነም። ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ዘመናዊ የአሳ ማስገሪያ እና ዘመናዊ ጀልባዎች አለመኖር ለአሳ ሃብቱ መቀነስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደምቢያ ወረዳ በአሳ ሃብት ተደራጅተው የሚሠሩ ወጣቶች ሕይወታቸውን በአሳ ሃብት እንደሚመሩ ተናግረዋል። ወጣቶቹ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም በአሳ ምርት እንደሚደግፉ ነው የገለፁት። በአሳ ምርት የተሠማረው ሙላቱ ጓዱ በጣና ሐይቅ ነጭ አሳ፣ ቀይ አሳና ቀረሶ እንደሚያሰግሩ ተናግሯል። አሳ እያሰገሩ እንደሚያስረክቡም ገልጿል።
ዘመናዊ ጀልባዎች ቢኖሯቸው ደኅንነታቸው ተጠብቆ የተሻለ ምርት ሊያመርቱ እንደሚችልም ገልጿዋል። ዘመናዊ የማስገሪያ መረብ እንደሌላቸውም ተናግሯል። መረቡ በባሕላዊ መንገድ የሚሠሩትና ከሱዳን የሚመጣ ጠባብ መረብ መኾኑንም አስታውቋል። ዘመናዊ መረብ እንዲቀርብላቸው ጠይቀው አለማግኘታቸውንም አስታውቋል።
ሌላኛው አሳ አስጋሪ ዋሴ ደረበ ጥሩ የአሳ ሃብት መኖሩን ገልጿል። በተለያዩ ምክንያቶች እየተቆራረጠባቸው እንጂ የአሳ ሃብቱ ጥሩ መኾኑንም ተናግሯል። ከሱዳን የሚመጣው መረብ ትንንሽ አሳዎችን አብሮ ከማውጣትም በላይ ረጅም ጊዜ እንደማያስጠቅምም ገልጿል። በብዙ ችግር ውስጥም ቢኾኑም በአሳ ሀብት ኑኖውን እንደሚመራ ነው የተናገረው። ኑሯችንም ጣና ነው የኑሮ መሠረታችንም አሳ ነው ብሏል። ዘመናዊ ጀልባዎች እና ዘመናዊ ማስገሪያ መረብ እንዲኖራቸው ብድር መጠየቃቸውን የተናገረው ዋሴ የጠየቁት ብድር ግን አለመፈቀዱን ነው የገለጸው።
የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ የእንሥሳት እርባታና መኖ ልማት ቡድን መሪ ተስፋሁን ዓለሙ በወረዳው በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በአሳ ሃብት ላይ በቋሚነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል። በጣና ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሕይወታቸው ከጣና ጋር የተያያዘ መኾኑንም አስታውቀዋል። በወረዳው አምስት በአሳ ሃብት ላይ የሚሠሩ ማኅበራት መኖራቸውንም ተናግሯል። ሌሎቹ መታወቂያ እየተሰጣቸው እንደሚያሰግሩም ተናግረዋል። ወረዳው በጣና ዳርቻ እንደመገኘቱ መጠን በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አይደለም ብለዋል።
ሕገወጥ የአሳ አስጋሪዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ መኾናቸውን የተናገሩት ቡድን መሪው ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አለመቻላቸውንም አስታውቀዋል። የተሻለ ምርት እንዲያመርቱና የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠር እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። አሳን ከጣና ሐይቅ ባለፈ በኩሬ ለመጠቀም እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እንስሳት እና አሳ ሃብት ፅሕፈት ኃላፊ ዶክተር ይበልጥ ተረፈ በዞኑ ከፍተኛ የኾነ የእንስሳት ሃብት መኖሩን ተናግረዋል። በዞኑ ከፍተኛ የኾነ የአሳ ሃብት አቅም መኖሩንም ገልጸዋል። በዞኑ ጣና ሐይቅ እና ሌሎች ታላላቅ ወንዞች ደግሞ ለአሳ ሃብት ታላቅ አቅሞች መኾናቸውን ነው የተናገሩት። መና፣ አንገረብ፣ ጓንግና ሌሎች ወንዞች አሳ ሀብት የሚመረትባቸው ታላላቅ ወንዞች ናቸው። በዞኑ ካላው የአሳ ሀብት አቅም አንፃር ተጠቃሚ አለመኾናቸውን ነው የተናገሩት። የአሳ ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥራትም በብዛትም እየቀነሰ ነውም ብለዋል። ዓመቱን ሙሉ መረብና ጀልባ ይዞ በጣና ሐይቅ ላይ መኖር የአሳ ሀብቱን ቀንሶታል ነው ያሉት። የማስገሪያ መረቦች ዘመናዊ አለመኾንም ለአሳ ሀብቱ ጥራትና ብዛት እንቅፋት ናቸው ብለዋል።
አስጋሪዎች በወንዞች ላይ የሚጠቀሙበት ኬምካል ምርቱን እየቀነሰው እንደኾነም ተናግረዋል። የአሳ ሃብቱን ጥራትና ብዛት የቀነሱትን ችግሮች ለመቀነስ እየሠራን ነውም ብለዋል። የእንቦጭ አረምም ለአሳ ምርቱ መቀነስ ምክንያት ኾኗል ነው የተባለው። በዞኑ አሳን ከሐይቅና ከወንዝ ባለፈ በኩሬዎች እና በግድቦች እያመረቱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የተቋሙ ተልእኮ የአሳ ግብርናን ማልመድና ማስፋፋት እንደኾነም ገልጸዋል። በአሳ ሀብት ደረጃ ትልቅ አቅም አለን፤ ባለን አቅም ልክ ግን በርካታ ምርት የለንም ነው ያሉት። በዓመቱ 6ሺህ 700 ቶን አሳ ለማምረት እቅድ ይዘው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ሕግወጥ የአሳ ማስገሪያ መረቦችን ከጉምሩክ ጋር በመተባበር ማቃጠላቸውንም ተናግረዋል። ያለ ወቅቱ አሳ በሚያሰግሩና ሕገ ወጥ የአሳ ማስገሪያዎችን በሚጠቀሙ ላይ እርምጃ እየወሰድን ነውም ብለዋል። ሕገወጥነት መከላከያ የሁሉም ሰው ተግባር ሊኾን እንደሚገባም ነው የተናገሩት። በዞኑ በጣና ዳርቻ በሚገኙ ወረዳዎች ሁሉ የአሳ ማኅበር መኖሩንም አስታውቀዋል። የብድር አቅርቦት ለሚጠይቁ ማኅበራት የብድር አቅርቦት እንደሚፈቀድም ገልጸዋል። የተነሳሽነት ችግር ካልኾነ በስተቀር ዘመናዊ የአሳ ማስገሪያ መረቦችን የማቅረብ ችግር እንደሌለባቸውም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!