
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ፌስትቫል እና ከንፈረንስ በአዲስ አበባ ኢትዮ ኩባ ፓርክ፤ በደሴ ደግሞ መርሆ ግቢ፣ ሆጤ ስታዲየም እና ወሎ የኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
በጥንታዊ እና ዘመናዊ የኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና ከነበራቸው አካባቢዎች መካከል ወሎ ግንባር ቀደሙ አካባቢ ነው፡፡ ሀገር በቀል እውቀት፣ ሃይማኖታዊ ትውፊት እና አብሮ የመኖር እሴት መስተጋብር ፈጥረው ዘመናትን የዘለቁበት ወሎ የጥበብ፣ የእውቀት እና የትምህርት ማዕከል ሆኖ አገልግሏል፡፡
የወሎን የትምህርት እና ሀገር በቀል እውቀት አበርክቶ የሚያወሳ እና የሚዳስስ በአይቱ የመጀሪያ የሆነ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ኮንፈረንስ እና ፌስቲቫል ይካሄዳል ያሉን በወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የወሎ ዩኒቨርሲቲ የባሕል፣ ኪነ-ጥበብ እና ሀገር በቀል እውቀት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዘላለም ጌትነት ናቸው፡፡
ወሎ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ኮንፈረሰንስ እና ፌስቲቫል ከታህሳስ 19/2015 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 23/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኢትዮ ኩባ ፓርክ ይካሄዳል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዘላለም ከታህሳስ 29/2015 ዓ.ም እስከ ጥር 7/2015 ዓ.ም ደግሞ በደሴ መርሆ ግቢ፣ ሆጤ ስታዲየም እና ወሎ የኒቨርሲቲ ግቢ ይካሄዳል ብለውናል፡፡
ኮንፈረንሱ እና ፌስቲቫሉ ወሎ ዩኒቨርስቲ ከቫይብራኒየም ሪሶርስስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የሚካሄድ ነው ያሉን የማዕከሉ ዳይሬክተር የወሎን ጥንታዊ እና ዘመናዊ አበርክቶ ከማውሳት ባለፈ በጦርነት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
በወሎ የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ኮንፈረንስ እና ፌስቲቫል ላይ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉ ምሁራን እና ታዋቂ ግለሰቦች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ያሉን ደግሞ ከቫይብራኒየም ሪሶርስስ ፋውንዴሽን ጋር በትብብር የሚሰሩት ዶክተር ሙሐመድ ሳኒ ናቸው፡፡ በኮንፈረንሱ እና ፌስቲቫሉ ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች ይኖራሉ ያሉት ዶክተር ሙሐመድ የተማሪዎች ትምህርታዊ ውድድር፣ የፈጠራ ሥራ ውድድር፣ የጉዞ መርሐ-ግብር፣ የፈረስ ትርኢት ፌስቲቫል፣ የባሕል ፌስቲቫል፣ ባዛር እና ፖስተር አውደ ርእይ፣ የሙዚቃ ዝግጅት እና ውይይቶች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዝግጅቱ የአካባቢውን የቱሪዝም አቅም መለየት፣ ማስተዋወቅ እና መዳረሻ ማድረግ፣ የሀገር አንድነት ላይ በተለይም ለወጣቶች ግንዛቤ መፍጠር እና የአካባቢውን አበርክቶ ለቀጣይ አቅም መነሻ ማድረግን ያለመ መሆኑን ዶክተር ሙሐመድ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!