
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምሁራን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ ሀሳብ በማፍለቅ በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
“የሀገረ-መንግሥት ግንባታና የምሁራን ሚና” በሚል ርእሰ ጉዳይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የምርምር ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ ሀገራዊ የምሁራን የምክክር መድረክ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል፡፡
ከ400 ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲ፣ የኮሌጅና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተመራማሪዎች፣ የምርምር ተቋማት ምሁራንና የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት የሚሳተፉበት ሀገራዊ የምክክር መድረክ በቀጣይ ጊዜያት ይካሄዳል፡፡
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም፤ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ምሁራን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የጋራ ጉዳዮችን ለማጉላት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ያላለቀ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምሁራን ከመጠላለፍ የፖለቲካ እሳቤ ወጥተው በእውቀት ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ አለባቸው ብለዋል፡፡
የሀገር ግንባታ የሚጸናው ጠንካራና ገለልተኛ ተቋም መገንባት ሲቻል በመሆኑ ምሁራን የአንበሳውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ምሁራን ከቀደመው ትውልድ የተገኘውን ሁለንተናዊ ድል፣ ሰላምና ነፃነት በሙያቸው የማስቀጠል ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
ከአክራሪነትና ከብሔር አጥር ወጥተው ለሁሉም የምትመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተቋማዊ ግንባታ ላይ አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት፣ የቀደምት ሥልጣኔ መገለጫና የአኩሪ ታሪክ ባለቤት በመሆኗ የሁላችንም ክብርና ኩራት ነው ብለዋል።
የ3 ሺህ ዓመት የሀገረ-መንግሥትና አስተዳደር ታሪክ ያላት ብትሆንም ጠንካራና ቀጣይነት ያላቸውን ተቋማት በመገንባት ሂደት ግን አለመሳካቱን አስታውሰዋል።
በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን ለመገንባት መንግሥት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
ለዚህ የመንግሥት ጥረት ስኬት በተለይም የምሁራን ሚና እና ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ምሁር ማለት የሕብረተሰቡን ችግር ተረድቶ በጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ምሁራን እውቀታቸውን ተጠቅመው ሕብረተሰቡን ከድህነት ማውጣትና ወደ ተሻለ ህይወት የሚሄድበትን አቅጣጫ ማመላከት አለባቸው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ምሁራን፤ በኢትዮጵያ የተቋማዊ ሥርዓትን ለመገንባትና ሀገረ-መንግሥቱን ለማፅናት እንቅፋት ሆኖ የዘለቀው ሁሉም የመንግሥት ሥርዓት ምሁራንን አግላይ ስለነበረ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሀሳብ ብቻ የሚያሸንፍበት አካሄድ እንዲኖር ምሁራን የሀሳብ መሪዎች በመሆን ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ሁሉ እገዛና ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል። ዘገባው ኢዜአ ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!