የኢትዮጵያ የዐይን ባንክ እስካሁን 1 ሺህ 9 መቶ በላይ ሰዎች የዐይን ብርሃናቸው እንዲበራላቸው ማድረጉ ተገለጸ።

104

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የዐይን ባንክ ከተቋቋመበት 1995 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 1 ሺህ 943 ሰዎች የዐይን ብርሃናቸው እንዲበራላቸው ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ታዬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት የኢትዮጵያ የዐይን ባንክ ከተቋቋመበት ሰኔ 1995 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 1 ሺህ 943 ሰዎች የዐይን ብርሃናቸው እንዲበራላቸው አድርጓል፡፡

በ1998 ዓ.ም አካባቢ በተጠና ሀገራዊ ጥናት መሠረት 300 ሺህ ገደማ ሰዎች የዐይን ብሌን እንደሚያስፈልጋቸው እና ይህ ቁጥር አሁን ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የዐይን ብሌናቸውን ቃል የገቡት የመጀመሪያው ሰው የኢፌዲሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ናቸው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የዐይን ብሌን ልገሳ በየጊዜው ቢኖርም አቅርቦቱና ፍላጎቱ ተመጣጣኝ አልሆነም ብለዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በአንዳንድ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ምክንያቶች በስፋት የዐይን ብሌኑን ሲለግስ አለመስተዋሉን አንስተው ከዚህ አስተሳሰብ በመውጣት የዐይን ብሌንን አፈር ከሚበላው በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖች ብርሃን እንዲሆን መነሳሳት ይገባል ነው ያሉት፡፡

አቶ ሀብታሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት የዐይን ብሌን ልገሳው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ሰው በፈቃደኝነት በሕይወት እያለ በሚገባው ቃል መሠረት እና በሕይወት እያለ ቃል ያልገባ ሰው ሲሞት ደግሞ የሟች ቤተሰብ ፈቃድ ሲገኝ የዐይን ብሌኑ ሊነሳ ይችላል፡፡

አንድ ሰው ሕይወቱ ካለፈ እስከ 8 ሰዓታት ውስጥ የዐይን ብሌኑ መነሳት እንዳለበት ገልጸው የማንሳቱ ሥራ እስከ 30 ደቂቃ ይጠናቀቃል ነው ያሉት፡፡

አንድ የዐይን ብሌን ከለጋሹ ከተነሳ በኋላ በ14 ቀናት ውስጥ ለሚለገስለት ሰው ቀዶ ጥገና መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
አገልግሎቱን የሚያገኙት የዐይን ብሌን ጠባሳ አጋጥሟቸው ዐይነ ስውር የሆኑ እንጂ በሌላ ህመምና አደጋ ምክንያት ለሚከሰት ዐይነ ስውርነት አለመሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የዐይን ብሌኑ ከተሰበሰበ በኋላ ከዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንዲሁም አዲስ አበባ የሚገኙ አራት የግል የዐይን ሕክምና ሰጪ ተቋማት፣ ጎንደር ስፔሻላይዝድ ማስተማሪያ ሆስፒታል፣ ጅማ ስፔሻይዝድ ማስተማሪያ ሆስፒታል እንዲሁም ሐዋሳ ስፔሻላይዝድ ማስተማሪያ ሆስፒታል በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት የዐይን ብርሃን ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቀዶ ጥገና ይሠራሉ፡፡

የዐይን ብርሃንን ለማንሳት ዋናው ነገር ብርሃን ያለው መሆኑን እና ከተነሳ በኋላም ለሚለገስለት ሰው የጤና እክል እንዳያመጣ በዐይን ብሌን እና በደም ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን ታሳቢ ያደረገ ምርመራ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በሽታ አስተላላፊ ተኅዋሲያን የሚገኙበት ሁኔታ ካለ የዐይን ብሌኑ ለሌላ ሰው ተላልፎ እንደማይሰጥም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያረጋገጡት፡፡ ዘገባው የፋብኮ ነው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገሪቱና ዘመኑ የወጣቶች ነው፣ በመኾኑም እኛ አርበኞች ታሪክን ማስተማር፣ ወደ መጥፎ መንገድ የሚሄዱትን ማስተካከል ይጠበቅብናል” ልጅ ዳንኤል ጆቴ መሥፍን
Next articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ መደበኛ ጉባዔውን ያካሂዳል።