“ሀገሪቱና ዘመኑ የወጣቶች ነው፣ በመኾኑም እኛ አርበኞች ታሪክን ማስተማር፣ ወደ መጥፎ መንገድ የሚሄዱትን ማስተካከል ይጠበቅብናል” ልጅ ዳንኤል ጆቴ መሥፍን

144

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ዓመታዊ ግምገማውን በባሕር ዳር እያካሄደ ነው።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መሥፍን የጥንታዊት ኢትዮጵያ አባቶች በተለያዩ ሥርዓት ሀገርን ለመውረር የመጣን ጠላት ለመመከከት አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ሊያስረክቡን ችለዋል ነው ያሉት።

ሀገርን የሚወር ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያውያን ያለማንም ቅስቀሳ በራሳቸው ተነሳሽነት እንደሚመክቱም ነው ፕሬዝዳንቱ የመሰከሩት። ፕሬዝዳንቱ “በየወቅቱ ሕዝቡ የሚያደርገው ተጋድሎ ኢትዮጵያ እንዳትከፋፈል ለማድረግ ነው” ብለዋል።

አሁንም ቢኾን ሀገርን የሚወዱ፣ በመልካም ሥነምግባርና በትምህርት የታነጹ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ መነካትን የማይፈልግና ክብሩን ማስጠበቅ እንደሚፈልግም ነው የተናገሩት።

“ሀገሪቱና ዘመኑ የወጣቱ ነው፣ በመኾኑም እኛ አርበኞች ታሪክን መንገርና ማስተማር፣ ወደ መጥፎ መንገድ የሚሄዱትን ማስተካከል ይጠበቅብናል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ የጥንት አርበኞች ቋንቋ፣ ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተጋድሎ ሲያደርጉ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ ከታለመለት ዓላማ እንዲደርስ ሁሉም ከልቡ መሥራት ይጠበቅበታል። ግልጸኝነት፣ ሁሉን ነገር እኔ እኔ ማለትን ማስቀረት ሀገራዊ ምክክሩን ሊያሳካው ይችላል ነው ያሉት። በታሪክም ቢኾን የሀገርን አንድነት ማስጠበቅ የተቻለው “እኛ” የሚለው ሀሳብ በመዳበሩ ነውም ብለዋል።

በግምገማው ላይ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ድኤታ አየለች እሸቴ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በስትራቴጂክ እቅድ በመመራት በዞንና በወረዳ ለሚገኙ አባላቱ ተደራሽ ለመኾን እያደረገ የሚገኘው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል። የማኅበሩን አባላት ፍላጐት ለማሟላት በተለይ ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ሚንስትር ድኤታዋ ጠይቀዋል።

ወይዘሮ አየለች እንዳሉት የአሁኑ ትውልድ በተሰማራበት መስክ ውጤታማ እንዲኾን የልማት አርበኛ ኾኖ መሥራት አለበት። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አስፈላጊውን ድጋፍ ኹሉ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሀገር ምልክት የኾኑትን አርበኞች ማክበርና መደገፍ ይገባል” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ የዐይን ባንክ እስካሁን 1 ሺህ 9 መቶ በላይ ሰዎች የዐይን ብርሃናቸው እንዲበራላቸው ማድረጉ ተገለጸ።