
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ የመሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ጥፋቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው እንዳሳሰበው የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ታላቁን የጣና ሐይቅ እና የዓባይን ወንዝ ተንተርሳ የተመሰረተች ውብ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል የቱሪስት ማዕከል ነች፡፡ ባሕር ዳር ከጢስ ዓባይ ፏፏቴ በቅርብ ርቀት 30 ኪሎ ሜትር አካባቢ ከባሕር ወለል በላይ በ1 ሺህ 700 ሜትር ከፍታ ላይ ከትማ ትገኛለች፡፡ የባሕር ዳር ከተማን ተፈጥሮ ውበት ብታጎናጽፋትም ውበቷን እና መሠረተ ልማቱን በመንከባከብ ረገድ እጥረት አለ፡፡ በተለይም በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች የሚስተዋሉ አግባብ ያልሆነ የመሠረተ ልማት አጠቃቀም፣ አያያዝ እና ጥፋት ቀጣይ የከተማዋ እድገት እንቅፋት ሆኗል፡፡
የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶ ገመዶች እና የመንገድ አካፋዮች መካከል ላይ የተተከሉ ዕጽዋትን ደኅንነት ለመጠበቅ የተተከሉት ብረታ ብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አብመድ ታዝቧል፡፡ ይህም የመንገድ ዳር መብራቶች አገልግሎት እንዲቋረጥ፣ ለከተማዋ ውበት ታስቦ የተተከሉ ዕጽዋትም ለጉዳት እንዲዳረጉ አድርጓል፡፡ በርካታ ሀብትም ለብክነት ተዳርጓል፡፡ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም ችግሩ በአፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠው ከተማዋን ለከፋ አደጋ ይዳርጋታል ነው ያሉት፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ሽምብጥ በመባል በሚጠራው ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ጋርዳቸው አንሙት ‹‹በብድር እና በልመና የተገነቡ መሠረተ ልማቶች የወጣባቸውን ወጪ ያህል አገልግሎት ሳይሰጡ ጠፍተዋል፤ ማታ ያየናቸውን ጠዋት ላይ እያጣናቸው ነው›› ብለዋል፡፡
ችግሩ የቅንጅታዊ አሠራር እጥረት እና አመለካከት ላይ ካለመስራት የመጣ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ መንግስት ህግ በማስከበር፣ ሕዝብ በመተባበር እና ብዙኃን መገናኛ ደግሞ ግንዛቤ በመፍጠር ቢሠሩ ችግሩን ማቃለል እንደሚቻልም ያምናሉ፡፡ ሕዝቡ አስተያዬት ለመስጠት ስጋት እንዳይፈጠርበትም ከተማ አስተዳድሩ ነፃ የስልክ አገልግሎት መጀመር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን በሚመለከት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ጽዳት እና ውበት ጽህፈት ቤት እና የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያን አነጋግረናል፡፡ የከተማ አስተዳድሩ የጣና ሐይቅን ተከትሎ ረጅም የእግረኛ መንገዶችን (ጣና ወክ ዌይ) በመብራት ለማስዋብ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማሠራቱን አስታውሷል፡፡ በየ35 ሜትር ርቀት ላይ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫቶች እንደተዘጋጁም ነው ያስታወቀው፡፡
በዋና ዋና መንገዶች ለከተማ ውበት የሚሆኑ የዘንባባ ተክሎችን እና ሳር በመትከል ለእይታ ማራኪ ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ካርታና ፕላን መነሻ አድርጎ አረንጓዴ ፖርኮችን ቢያለማም በተፈለገው ልክ አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚያደርጉ ህገ ወጥ ተግባራት እየተበራከቱ መምጣታቸው ልማቱን ፈታኝ አድርጎታል ነው የተባለው፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ጽዳት እና ውበት ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጌታሁን “በተለይም ለከተማዋ ደረጃ እና ለሕዝቡ ስነ ልቦና የማይመጥኑ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ከጽህፈት ቤታችን አቅም በላይ ሆኗል” ብለዋል፡፡ ህገ ወጥ ተግባራትን በመከላከል በኩል የሕብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት ዝቅተኛ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የመብራት ገመድ እና በየቦታው የተተከሉ ብረታ ብረት እየተነቀሉ እየተወሰዱ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ እና ከተማ አስተዳድሩ በጋራ ጥረት ማድረግ ካልቻሉ ችግሩ በከተማዋ ህልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ መሆኑን አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ ቦታዎችን በአረንጓዴ ልማት ለማስዋብ ከተማ አስተዳደሩ በጀት መድቦ ወደ ሥራ መግባቱም ታውቋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ችግሩ በስፋት መኖሩን አምነዋል፤ ተቀናጅቶ የመሥራት ክፍተቶች የፈጠሩት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በከተማዋ መሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ጥፋቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል›› ያሉት መምሪያ ኃላፊው ችግሩ በፖሊስ ጥረት ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን፣ ለመፍትሔውም መጠነ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ እና አጋርነት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ለችግሩ ለሚመጥን መፍትሔ ከሕዝቡ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ኃላፊው ነግረውናል፡፡
ይህ ሁሉ ጥፋት ተፈጽሞ በጉዳዩ ተጠርጥረው የተያዙ ወይም ቅጣት የተላለፈባቸው አካላት አለመኖር ደግሞ በክትትልና ሀብትን በመጠበቅ በኩል ክፍተት መኖሩን ያሳያል፡፡ በከተማዋ የመሠረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል እንደሆነ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው