“ከጀግኖቹ ሀገር፣ ከበለሳ ሰማይ ሥር”

219
Made with LogoLicious Add Your Logo App

ጎንደር: ታኅሣሥ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለጀግንነቱ ልክ የት ይገኛል? ሀገር ተደፈረች ሲባል በጦር ሜዳ ቀድሞት የሚደርስ የት ይኖራል? በተመቸም ባልተመቸም ዘመን ሀገሩን የሚወድ ማንስ ከእርሱ በፊት ቀድሞ ይጠራል? እንደርሱ ተኩሶ መምታት የተሳካላት ከወዴት ይገኛል? አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት የሚያድል፣ በጀግንነቱ ሀገርን የሚያደላድል፣ ጠላቱን ከወገኑ ለይቶ የሚጥል ነው። ምድሩ ልቡ ላይ የታጠቀ ጀግና ይወለድበታል፣ ፍርሃት ያልፈጠረበት ጎበዝ ያድግበታል፣ አድጎ ይጎመራበታል፣ ቢሻው በዋልካው፣ ቢሻው በተራራው፣ እንዲያም ሲል በሸለቆው እየተመላለሰ ይኖርበታል፣ የጀግንነት ልኩን፣ የሀገር ፍቅር ወጉን፣ የአይደፈሬነት ምስጢሩን ይማርበታል።

እኒያ ጀግኖች በተራራዎቹ፣ በሸንተረሮቹ፣ ሜዳና ሸለቆዎቹ መውዜራቸውን አንግተው፣ ቤልጅጋቸውን ወልውለው፣ ጎፈሬያቸውን ነቅሰው፣ ትጥቃቸውን አሳምረው በልበ ሙሉነት ይመላለሳሉ፣ በኩራት ይታያሉ፣ ሀገር ሰላም በኾነ ጊዜ በሚያምሩ በሬዎቻቸው ወደ ዋልካው ወርደው፣ ወደ ተራራው ወጥተው፣ ወደ ሸለቆው ተጉዘው ያርሳሉ፣ በሰፊ አውድማ ያፍሳሉ። ደጎች ናቸው እንግዳ በልቶ የጠገበ የማይመስላቸው፣ ጀግኖች ናቸው ጠላት የማይደፍራቸው። እኒያ ጀግኖች “አዝማች እንጂ አድማጭ የለንም” ይላሉ። ክፉ ቀን በመጣ ጊዜ ያዘምቷቸዋል፣ ከፊት አስቀድመው ያዋጓቸዋል፣ ሰላም ሲኾን ጀሮ ይነሷቸዋልና። ጀግኖቹ ሲያዘምቷቸው በጀግንነት ይዋጋሉ፣ ያዋጋሉ፣ ጠላትንም ድል ያደርጋሉ።
የዚያች ምድር ጀግና ሀገር ተነካች በተባለ ቁጥር ሞፈርና ቀንበሩን እየሰቀለ፣ መውዜርና በልጅጉን እየወለወለ፣ ሳንጃውን እያሾለ፣ ጎራዴውን እየሳለ ይነሳል፣ በደሙ ጠብታ ሀገር ያፀናል፣ በአጥንቱ ክስካሽ ወገኑን ያኮራል። እርሱ ወድቆ ሠንደቅ ያቆማል፣ እርሱ ወድቆ ሀገር ያፀናል፣ የማይሻር ታሪክ ይፅፋል። ክፉ ቀን በመጣ ጊዜ የሚያዘምታቸው ይበረክታል፣ ሰላም በመጣ ጊዜ የሚሰማቸው ይጠፋል። በጭንቅ ቀን የተጠለሉበት በሰላም ጊዜ ይረሱታል፣ በቸገራቸው ጊዜ የጎረሱበት ቸገረኝ ባላቸው ዘመን ዝም ይሉታል፣ በተጠሙ ጊዜ ያጠጣቸው ጠማኝ ሲላቸው ውኃ ይነሱታል፣ ክፉውን ዘመን መንገድ ኾኖ ያረማመዳቸው፣ ድልድይ ኾኖ ያሻገራቸው መንገድ አሳዩኝ ሲላቸው ጀሯቸውን ይመልሱበታል፣ ሕይወቱን ሰጥቶ ከፍ ከፍ ያደረጋቸው ከከፍታቸው ላይ ኾነው ወደታች ለመመልከት ይረሱታል፣ የት እንደነበር ይዘነጉታል።

አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ስማቸው ሲነሳ ታሪክ አብሯቸው የሚነሳ፣ አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ስማቸው ሲወሳ ጀግንነት አብሯቸው የሚወሳ፣ አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ሲታወሱ ጀግንነት፣ ታማኝነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ አሸናፊነት፣ ዓልሞ መችነት አብረው የሚነሱ። በለሳ በተነሳ ቁጥር ጀግንነት፣ ታማኝነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ አሸናፊነት እና ፊት መሪነት አብሮ ይነሳል።

ወደ በለሳ ሄጄ ነበር። ገና ወደ በለሳ እንደምሄድ ባወኩ ጊዜ ልቤን ሀሴት መላት። ነብሴን ደስታ አስጨነቃት፣ ጀግና የሚፈጠርባቸውን፣ ጎበዝና ጎበዝ የሚገኝባቸውን ሥፍራዎች ማየት፣ ከእነርሱም ጋር መሰንበት ከደስታም በላይ ደስታ ይሰጣልና። የጀግኖችን ሀገር እንደምረግጥ ባወኩ ጊዜ ደስታዬ ወሰን አጣች። ልቤ ጮቤ ረገጠች። ጀንበር በምሥራቅ መስኮቷ እየተፍለቀለቀች ነው። በጠራው ሰማይ ላይ ስትፍለቀለቅ ከጫጉላ ቤት የወጣች ሙሽራ ትመስላለች። በደንገጡሮች ታጅባ፣ በፊትና በኋላዋ፣ በግራና በቀኟ በፈረስ ላይ በተቀመጡ ጦረኞች ተከብባ፣ ሽቶ እየተርከፈከፈላት፣ መለከትና እንቢልታ እያጀባት፣ ድባብ ተዘርግቶላት፣ ቀሚሷ አፈር እንዳይነካ በአገልጋዮቿ እየተሰበሰበላት፣ የበዛ ሕዝብ እጅ እየነሳላት ከቤተ መንግሥት የምትወጣ ንግሥትም ትመስላለች።
ተውባ ለምድር ብርሃን ሰጥታለች፣ አጊጣ ምድርን አስጊጣታለች። ያለሁባት መኪና በጠጠር መንገድ እየነጠረች እየተጓዘች ነው። የልቤ ፍጥነት መኪናዋን ቀድሟት ከተጓዘች ቆይታለች፣ ልቤ መዳረሻዬ በኾነችው ምድር አስቀድማ ተወስዳለችና የመንገዱን አለመመቸት ልብ አላላችውም። መኪናዋ ወጣ ገባውን መንገድ እየሰነጠቀች እየገሰገሰች ነው። ከልቤ ፍጥነት ግን መድረስ አልተቻላትም። ለምን ልቤ አስቀድማ ካሰበችው ሥፍራ ደርሳለችና። ያቺ በማለዳ እየተፍለቀለቀች በውበት ልብን የምትሰርቀው ጀንበር ኃይለኛ መኾን ጀምራለች። ወደ ልቤ መዳረሻ ምድር ልደርስ ነው። ጉጉቴ የበለጠ ጨምሯል። ምድሩ በአሻገር ይታይ ጀምሯል። ጋራና ሸንተረሩ፣ ሜዳና ገደሉ እየተጣራ ነው። “ቧልት አያውቅም እንጂ ቁም ነገር አይረሳ የእነ ስበር ሀገር እንዴት ነው በለሳ” በለሳ ከጀግኖቹ ምድር፣ ከአይደፈሬዎች ሀገር፣ ከልበ ሙሉዎች አድባር ደርሻለሁ። ልቤ የጓጓችላትን፣ በሀሴት የፈነደቀችላትን ምድር ነክቻለሁ። የልቤን ምድር አይቻለሁ።

የመጀመሪያ መዳረሻዬ በለሳ ጉሃላ ነበር። ዘመን የደረሰበትን፣ መንገድ የሚዋብበትን አስፋልት አዲስ ዘመን ከተማ ላይ ከተለየሁት ቆይቻለሁ። አስፋልት ከአዲስ ዘመን በኋላ ላለው ሕዝብ የተፈቀደና የተገባ አይመስልም። በበለሳ ሰማይ ሥር ጉሃላ ከደጋጎቹ ጋር ተቀላቅያለሁ። ሰው አክባሪነት እና እንግዳ ተቀባይነት የእነርሱ ናቸው። በፈገግታቸውና በደግነታቸው አስረውኛል። ከጉሃላ በአሻገር በኩራት የሚታየውን ዞዝ አምባን ተመለከትኩ። ከተራራው ግርጌ አምሳለ ላልይበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት የኾነ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ይገኛል። ከተራራው አናት ላይ ደግሞ ያገኘ ሁሉ የማይወጣበት፣ በበዓት የተወሰኑ ዝጉሃን አበው ብቻ የሚኖሩበት ድንቅ ደብር አለች። አንጓ ተረራ፣ ጨውጫውት፣ ደንጎራ፣ አጭቃን የተሰኙ ድንቅ ውበትን የተላበሱ ተራራዎች ይታያሉ። የበለሳ ተራራዎች ዝም ብለው ተራራዎች አይደሉም። የከበሩ ታሪኮች የተሠሩባቸው፣ በየዘመናቱ ጀግኖች የተመላለሱባቸው፣ ጀግና የመላባቸው ናቸው እንጂ።

ወደ ዙይ ሀሙሲትም ወረድኩ፣ በዚህ ሁሉ ጉዞዬ ከተሞች ውስጥ ለዐይን መያዝ መከላከያ ( ትራኮማ) ከተሠሩት ደረጃቸው ከወረዱ አስፋልቶች በስተቀር አስፋልት የሚባል አልገጠመኝም። እነዚያን የመሠሉ ጀግኖች፣ እነዚያን የመሠሉ ደጎችና ኩሪዎች አቧራ እየቦነነባቸው፣ ዛሬም እንደቀደመው ዘመን በእግራቸው ይጓዛሉ፣ ከቦታ ቦታ ሲጓጓዙ ሥንቅ እየቋጠሩ፣ በመንገድ እያደሩ በእግራቸው ይኳትናሉ፣ መሥዋዕት በከፈሉባት ሀገራቸው በአሻቸው ሰዓት እንደ አሻቸው የሚሄዱበት ተሽከርካሪ የለማ። ተሽከርካሪዎች ቢኖሩ እንኳን በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ ማግኘት አይችሉም። በረሃና ሸንተረሮችን በእግራቸው እያቆራረጡ አድካሚውን ሕይወት ይገፋሉ። ወደታች በወረዱ ቁጥር ጀግኖች የሚወለዱባቸው የበለሳ ቆላማ ሥፍራዎች ሞልተዋል። አርባ ፀጓር እና ሌሎች ስመ ጥር ቆላማ ሥፍራዎች። ከበለሳ አባቶች እግር ሥር ተቀምጨ ስለ በለሳ ብዙ ሰማሁ።

ጋሽ ላቂያው በዛብህ ስለ በለሳ ብዙ ነግረውኛል። አይ በለሳ ድንቅ ምድር። በለሳ በነገሥታቱ አይሰግ እና ደባሪ፣ ዙይ እና ዘሃዬ ተብሎ በምክትል አሥተዳዳሪ ይተዳደር ነበር። ሀገረ ገዢዎች ከመናገሻዋ ከተማ ጎንደር እየተነሱ ወደ በለሳ እየወረዱ ሀገር ያስተዳድሩ ነበር። በለሳም እየቆዩ ወደ መናገሻዋ ከተማ ይመለሳሉ። ሽንብራና ጤፉ፣ ማርና ቅቤው ሙሉ ነውና ይጫናል።
የበለሳ ጀግኖች ኢትዮጵያን ለመድፈር በመጡ ጠላቶች ላይ ሁሉ እጃቸውን አሳርፈዋል፣ የጣሊያን ወራሪ ድባቅ መትተዋል፣ ከዚያም በፊት ኾነ ከዚያም በኋላ ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩ ጀግኖች የሚፈጠሩበት ምድር ነው በለሳ። አያሌ የከፉ ጊዚያትን አሳልፈዋል። የበለሳ ጀግኖች በኢትዮጵያ ላይ ለውጥ ለማምጣት ደም እየገበሩ ታግለዋል፣ አታግለዋል። ዳሩ የትግሉን ፍሬ የሰጠው፣ የደሙን ዋጋ የከፈለው የለም። አብሯቸው የታገሉትም አላዩትም፣ በመከራቸው አብሯቸው የነበሩት በድሎታቸው ዘመን ቀና ብለው አልተመለከቱትም። የበለሳ ሕዝብ አንድ ልብ አንድ ወጥ ሃሳብ ነው ያለው፣ ላመነበት ነገር ግንባሩን ይሰጣል፣ በፍፁም ወደ ኋላ አይመለስም ነው ያሉኝ ጋሽ ላቂያው። አዎን በለሳ ላመነበት ነገር ጦር አይመልሰውም። ምሽግና ባሩድ አያስቆመውም። በዚያው ሰነበትኩ። ጋራና ሸንተረሩን እያቆራረጥኩ ድንቁን ምድር ተመለከትኩ።

“እንፍራንዝ ማክሰኝት ቁልቋል በር ሲነሳ ወረድ ወደቆላው አርባያ በለሳ” ወደ ተባለላት፣ ወደ አርባያም ገሰገስኩ። አርባያ ስሟ ከፍ ብሎ የሚጠራ የጀግኖች መገናኛ ናት። በለሳ ሲወርዱ ዋልካውን፣ ተራረውን፣ ሸንተረሩን እያማረጡ ያያሉ። እኔም ልዩ ልዩ ውብ ገፅታ ያለበትን ምድር እየተመለከትኩ ወደ አርባያ አዘገምኩ። በመንገዴ ላይ የበለሳ ጀግኖች እንደ ቀደመው ዘመን ሁሉ በእግራቸው ሲኳትኑ እየተመለከትኩ ነው። በለስ የቀናቸው ደግሞ በጭነት መኪና ተጭነው ወይም በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተጫጭነው፣ ግፋ ሲል ኮርቶ መጋላ ላይ ወጥተው ይጓዛሉ። በበለሳ ሰማይ ሥር የመሠረተ ልማት ዓይኖች ተመልክተው አያውቁም። ዙይና ዘሃዬ አይሰግና ደባሪ የሚገናኙበት የበለሳ ጀግኖች ጠጥተው ካደጉበት መና ወንዝ ደርሻለሁ።
ብዙዎች ስለ መና ተቀኝተውለታል፣ የበለሳ ልጆች ጠጥተው አድገውበታል፣ እየተራጩ ተዝናንተውበታል።

“ሀገሬ በለሳ ኧረ መና ወንዙ ውኃው ይጣፍጣል ማር እንደበረዙ” ተብሎለታል። ጋሽ ላቂያው መና የከፋው ሰው መጠጊያ፣ ሲጠማ የጥም መቁረጫ ነው ይሉታል። በለሳ ተወልዶ የመናን ውኃ ጠጥቶ ያላደገ ምኑን የበለሳ ልጅ ኾነም ይባላል ነው ያሉኝ። መና ስመ ገናናው ወንዝ። በለሳ
“አይደለም ጓንዴውን ቤልጅጉን ሲያነሳ፣
መቸ ይደፈራል ቆፍጣናው በለሳ” የተባለለት የአባቶቻችን የኩራት ምንጭ እኛም እየተከተልነው የመጣን፣ ልጆቻችንም የሚከተሉት ነውም ብለውኛል። በበለሳ ለሀገር የሚሳሳ የለም። ሀገር ስትነካ ታላላቅ አርበኞች የሚነሱበት የጀግና ሀገር ነውም።

ከስመ ገናናዋ አርባያ ደርሻለሁ። ዙሪያ ገባውን እየተመለከትኩ ከደጋጎቹ ጋር መልካሙን ጊዜ አሳለፍኩ። ጀግኖቹ ለሀገር በከፈሉት መስዋእትነት ልክ ልማት ያላያቸው፣ የመንገድ ችግር ያሰቃያቸው ናቸው። የበለሳ ጀግኖች የመሠረተ ልማት ችግር ቢጠናወታቸውም ከሀገር ፍቅራቸው እና ከጀግንታቸው ግን ዝንፍ አይሉም። ከጅግኖቹ ሀገር ከበለሳ ሰማይ ሥር ያላየሁት የለም። በፍቅር የተቀበሉኝን፣ ተቀብለው ያስተናገዱኝን፣ አቀማጥለው ያኖሩኝን ጀግኖቹን እና ደጎችን የምለይበት ጊዜው ደረሰ አርባያ በለሳን ወደኋላ ትቻት ፊቴን ወደ መናገሻዋ ከተማ ጎንደር አዞርኩ። የበለሳ ጀግኖች ቅንነት፣ ደግነት እና ጀግንነት ግን ከእኔ ጋር አልተለዩም።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተማሪዎችን በየደረጃው በብሔራዊ ደረጃ መመዘን ሀገራዊ ዝግጅቱን ለመገምገም ያግዛል” ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ።
Next article“የሀገር ምልክት የኾኑትን አርበኞች ማክበርና መደገፍ ይገባል” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)