አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡

235

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት መግለጫ አንዳሉት የአሜሪካ አፍሪካ ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ውይይቶችን እያካሄዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒዎ ብሊንከን እና ከአሜሪካ መንግሥት የደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ጋር መክረዋል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር አንደምትፈልግም መገለጹን አምባሳደር መለስ አስረድተዋል፡፡ ከሕወሓት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማብራሪያ እንደሰጡ የገለጹት ቃል አቀባዩ የአሜሪካ መንግሥት የሥራ ኀላፊዎች አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እና ትብብር ለማጠናከር እና ለማደስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን ነው ያስገነዘቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የዓለም ባንክ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲኾን 745 ሚሊዬን ዶላር የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

አምባሳደር መለስ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት አምባሳደሮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸው በተሰጠው ማብራሪያ የአውሮፓ ሀገራት ለኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች ላይ ድጋፍ የሚያደርጉ መኾናቸውንና ግንኙነቱን ለማጠናከር ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንዳለ መግለጻቸውን ነው ያስረዱት፡፡ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በበኩላቸው ጉዳዩ ጦርነት ከማቆም በላይ ብዙ የመልሶ መቋቋም ጥረቶች እና ድጋፎች የሚያስፈልጉት መኾኑን መገንዘባቸውንም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።

በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የባቡር መሰመር ለመዘርጋት ጥናት እየተደረገ ሲኾን ጥናቱን አስመልክቶ በካርቱም ውይይት ተደርጓል ያሉት አምባሳደር መለስ ይህም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ትብብር እና መቀራረብ እየመጣ ለመኾኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእኛ ሰው በሞሮኮ!
Next articleበኩር ጋዜጣ – ታኅሣሥ 10/2015 ዓ.ም ዕትም