
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የተቀበላቸውን ተማሪዎች እንደ ወላጅ ሆኖ ከሱስ አምጭ ዕፆች ለመጠበቅ እየሠራ መሆኑን አመለከተ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የሚመለከታቸው አካላትም የዩኒቨርሲቲውን አካባቢ የንግድ እንቅስቃሴ በተለዬ ሁኔታ እየተከታተሉ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው መከፈት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ያስገኘ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ባሕል ያፈነገጡና ከዚህ ቀደም በስፋት ያልተለመዱ በጥብቅ የሚከለከሉ ድርጊቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ እምብዛም ያልተለመዱ እና የሕዝቡን እሴት የሚሸረሽሩ ነገሮች እንደ አዲስ ብቅ ማለታቸውም የአካባቢውን ማኅበረሰብ አሳስቧል፡፡ በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ ጫት የሚያስቅሙ፣ መጠጥ የሚሸጡ እና ሽሻ የሚያስጠቅሙ አካላት መኖራቸውን በአካባቢው የሚኖሩ ግለሰቦች ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ጥሩዬ አግማስ እና ዮሐንስ ስጦታው እንደተናገሩት ድርጊቱን ከሚፈጽሙት አካላት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማው ያቀኑ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በተለይም ጫት መቃምና ሽሻ ማስጨስ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ እሴት እና ሞራል የማይመጥኑ በመሆናቸው ሳይሰፉ በፍጥነት ማስተካከያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ በከተማው እየታዬ ያለው የጫት ማስቃም እና ሽሻ ማስጠቀም ተግባር በማኅበረሰቡ እና በሃይማኖት አባቶች በጥብቅ የሚወገዝ ተግባር ነው፡፡ ይህንን መጤ እና ጎጂ ድርጊት ሳይስፋፋ በፍጥነት ለማጥፋት ዝግጁ መሆናቸውን እና መንግሥት በባለቤትነት ይዞ በቅርብ ሊከታተል እንደሚገባ ነው አስተያዬት ሰጭዎቹ የተናገሩት፡፡
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው ምሥራቅ በትምህር ተቋማት አቅራቢያ የሱስ ተጋላጭነትን የሚያበረታቱ ተግባራት እንዳይከናወኑ በሕግም ጭምር የሚከለከል ነው፤ ጫት ቤት መክፈት፣ ሽሻ ማስጠቀም እንዲሁም የመጠጥ እና የጭፈራ ቤቶች በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ ፈጽሞ መኖር እንደሌለባቸው ነው የሚገልጹት፡፡ በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ የመሠል ድርጊቶች መስፋፋት የዩኒቨርሲቲውን ስም ጥላሸት የሚቀቡ በመሆናቸው መፍትሔ እንዲሰጣቸው በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ዓመት ድርጊቱ እንዳይኖር ከፖሊስ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ይሄነው ጎጅ ድርጊቶችን ለመከላከል የዩኒቨርሲቲውን መተዳደሪያ ደንብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለተማሪዎች የግንዛቤ ፈጠራ እና የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
የምቃራ ቀበሌ ፖሊስ ‹ኦፊሰር› ሳጅን የሱፍ ጡሃዬ በበኩላቸው ሰባት ግለሰቦች ዩኒቨርሲቲውን መሠረት አድርገው ጫት በማስቃም እና ሽሻ በማስጨስ ሥራ ተሰማርተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ ግለሰቦቹ ትክክል አለመሆናቸውን በመምከር ሥራውን እንዲያቆሙ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ በተያዘው ዓመትም ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት በዩኒቨርሲቲው አካባቢ እነዚህ ተግባራት እንዳይከናወኑ የአካባቢውን የማኅበረሰብ አባላት እና ከ300 በላይ ወጣቶችን ያሳተፈ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፀጥታ ኃይሉ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም በቅንጅት ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡ በዚህ አካባቢ መጠጥ የሚሸጡ አካላትም በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል›› ብልዋል፡፡
የደባርቅ ወረዳ ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አገናኘው ማሙዬ በማኅበር ተደራጅተው ለሕጋዊ ሥራ የወሰዱትን ቦታ በማኅበረሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያስከትል በሚችል መቀየር ተገቢ ባለመሆኑ ይህን የሚሠሩ እና የሚያሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በተፈቀደላቸው የአገልግሎት፣ የንግድ እና ማኒፋክቸሪንግ ሥራ ላይ ብቻ እንዲሠማሩም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ከዚህ ውጭ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው እና ጎጅ ሥራ በሚሠሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ