ʺሞተውም ይኖራሉ፣ አልፈውም ያኮራሉ”

259

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለተጨነቁት የደረሱት፣ በጨለማው ዘመን ብርሃን የኾኑት፣ ጥቁሮችን ያኮሯቸው፣ ነጮችን ያንበረከኳቸው፣ በክብር ላይ የመጡትን የቀጧቸው፣ ጭቁኖችን ያኮሯቸው፣ ቀኝ ገዢዎችን በብልሃት፣ በጥበብና በጀግንነት የጣሏቸው እምዬ ሆይ ሞት እንደምን ቻለዎ? ኀያላኑ ድምጽዎን ሰምተው የደነገጡት፣ ግርማዎትን አይተው የተርበደበዱልዎት፣ ጦር ከእኛ በላይ ላሳር ያሉት እጅ የነሱልዎት፣ ለጥቁሮች ምልክት የኾኑት፣ በጥቁሮች ምድር ይቻላልን ያሳዩት፣ ለዘላላም በማይወርድ ከፍታ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሠንደቅ ያውለበለቡት፣ ለስልጣኔ፣ ለከፍታ፣ ለአንድነት እና ለክብር የተጉት እምዬ! የማሸነፊያውን መንገድ ያሰመሩት፣ አሸናፊውን ጦር የመሩት፣ በአሸናፊነትም የተመላለሱት፣ በድል አድራጊነት የተከበሩት አባ ዳኛው ሞትዎ በተሰማ ጊዜ ሀገር ደንግጣለች፣ አፍሪካ አልቅሳለች፣ የነጻነቴን መሪ፣ የአሸናፊነቴን ፊት አውራሪ ተነጥቄያላሁ ብላለች፡፡
ለምን ከተባለ የጀግና ሞቱ ያስፈራል፣ ያስደነግጣል፣ ጥቁር ማቅ አስለብሶ ያስለቅሳልና፡፡ የጀግና ሞቱ ለሀገሩ፣ የጀግና ሞቱ ለሕዝቡ አስደንጋጭ ነውና፡፡ ጥቁሮች ማሸነፍን የተማሩባቸው፣ እንችላለንን ያዩባቸው፣ ድል አድራጊነትን ያረጋገጡባቸው ኃያል ንጉሥ ናቸውና ሀዘኑ ከባድ ነበር፡፡

ነጻ በኾነች ሀገር የነገሡት፣ የአባቶቻቸውን ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁት፣ ለሀገር የተከፈለውን መስዋእትነት የሚገነዘቡት፣ ባሕላና እሴቶቻቸውን፣ ሃይማኖትና ታሪካቸውን የሚያከብሩት፣ በብልሃት የሚራመዱት፣ በጥበብ የሚኖሩት ኃያሉ ንጉሥ ስማቸውን ጠላቶቻቸውም ወዳጆቻቸውም አነሱት፡፡ ለምን እሳቸው ጠላት የሚፈራቸው፣ ወዳጅ የሚኮራባቸው፣ የሚመካባቸውና የሚከበርባቸው ናቸውና፡፡
ከመኳንንቶቻቸው፣ ከጦር መሪዎቻቸው፣ ከእልፍኝ አስከልካዮቻቸው፣ ከቅርብ አገልጋዮቻቸው ጋር እየመከሩ ለሀገር ክብር ታተሩ፣ ለሀገር እድገት ያለ ድካም ሠሩ፣ በተከበረች ሀገር የተከበረ ታሪክ ጽፈው ያልፉ ዘንድ በቅንነት፣ በታማኝነት እና በጀግንነት ኳተኑ፡፡ መልካም ስም ከመቃብር በላይ እንደሚውል አስቀድመው ያውቃሉና የከበረ ሥራቸውን እና የማይጠፋ ስማቸውን በምድር ጥለው ያልፉ ዘንድ መልካሙን አደረጉ፡፡

ተወልደው ያደጉባት፣ በሜዳዎቿ ፈረስ ጉግሰስ የተጫወቱባት፣ ጦር ውርወራ የተካኑባት፣ በክብርና በሞገስ ያደጉባት፣ በኋላም በረቀቀ የክብር ልብስ ተውበው፣ ከከበረው ዙፋን ላይ ተቀምጠው፣ የወርቁን በትረ መንግሥት ጨብጠው የነገሡባት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለክብሯ የሚመጥነውን ሁሉ አደረጉ፡፡ ለክብሯ የሚመጥናት በጠላት ሳትደፈር መኖር ነውና ጠላቶቿን ቀጥተው አስከበሯት፣ ለክብሯ የሚመጥናት ነጻ ኾና መኖር ነውና ጠላቶቿን ቀጥተው በነጻነት የደመቀች፣ የነጻነትም ጀንበር የኾነች፣ የነጻነት ምልክት የተባለች ሀገር አደረጓት፡፡

ምኒልክ ጀግና የጦር መሪ ብቻ አይደሉም፣ ታላቅ የስልጣኔ አባት ጭምር እንጂ፡፡ እርሳቸው መልካሙን ሁሉ አድርገዋል፣ የስልጣኔውን በር ከፍተዋል፣ በሀገራቸው የስልጣኔ ፍሬዎችን አሳይተዋል፡፡ አፄ ምኒልክ ዓድዋን የሚያክል ከተራራ ሁሉ የገዘፈ፣ በረቀቀ ቀለም የተጻፈ፣ በማያረጅ ብራና ላይ ያረፈ ታሪክ የጻፉ፣ ያስጻፉ ኃያል ናቸው፡፡

ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ግሊክን የተባለን ጸሐፊ ጠቅሰው ሲገልፁ ʺ አሳባቸው በመልካም ሁኔታ እያስተዳደሩ የሀገራቸውን እድገት ማፋጠን ነው፡፡ ምኒልክ የተከበሩ በጣም ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ ታዋቂነታቸው በፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ የሳይንስ ውጤት በኾኑ ጥበባዊ ሥራዎችም እውቅ ናቸው፡፡ ምኒልክ ሩህሩህ ነበሩ” ብለዋል፡፡
ወረኃ ታኅሣሥ ገብቷል፡፡ ወሩ በገባ በሁለተኛው ቀን ሊቃውንቱ ለበዓለ በዓታ በየአድባራቱና በየገዳማቱ ዋዜማ ቆመዋል፡፡ አድባራቱና ገዳማቱ በሊቃውንቱ ተመልተዋል፡፡ አበው ሲመርቁ ጳጳሱን ከመንበሩ፣ ንጉሡን ከዙፋኑ ያጽናልን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያን ሰላም ያደርግልን፣ ዳሯን እሳት መሀሏን ገነት ያድርግልን ይላሉ፡፡ ቀሳውስቱ፣ መነኮሳቱ፣ ዲያቆናቱ፣ መዘምራኑና አንባብያኑ ሁሉ በአጸዱ ሥር ተጸልለዋል፤ ከበሮው ይመታል፣ ጽናጽኑ ይንሿሿል፣ ዝማሬውና ምስጋናው ከፍ ብሏል፡፡

ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሁሉ አላንቀላፉም፣ በጊዜ እንደቆሙ በዝማሬና በምስጋና አደሩ እንጂ፡፡ ዝማሬውና ምስጋናው ሳይቋረጥ፣ ሊቃውንቱም ሳይደክሙ ነጋ፡፡ ሊቃውንቱ በምስጋና ባደሩበት፣ ምዕምናኑም ነጫጭ እየለበሱ የካሕን ድምጽ ወደሚሰማበት አጸድ ሥር በሚሰባሰቡበት ጊዜ በቤተ መንግሥት ታላቅ ሀዘን አንዣብቧል፣ አባ ዳኛው እንደ ወትሮው በታላቅ አጀብ ወደ ቤተ መቅደስ አልተጓዙም፣ ካማረው አልጋቸውም አልተነሱም፣ እርሳቸው በደኅናቸው ያን በመሰለ ቀን ከቤተ መቅደስ አይርቁም፣ ካሕናቱም ይጠብቋቸዋል፣ ምዕመኑም ይናፍቃቸዋል፡፡ በዚያ ጊዜ ግን ሕመማቸው በርትቷል፣ እቴጌ ጨንቋቸዋል፣ የቤተ መንግሥት አሽከሮች፣ መኳንንቱና የጦር አበጋዞች ሐዘን ይዟቸዋል፤ የበረታው ሕመማቸው ከዛሬ ነገ ይሻላቸዋል ሲባል የከፋ ኾኖ የመጨረሻዋ ቀን ደረሰች፡፡

እኒያ መልካም ቃላትን የሚያወጡ ልሳናቸው ዝም አለች፣ እኒያ ጥበብን ያማተሩ ዓይኖቻቸው ተከደኑ፣ እኒያ ብርቱ ክንዶቻቸው ዛሉ፣ እኒያ ዳገት ቆልቁለቱን የወረዱበት፣ ሜዳውን የሮጡበት፣ ረጅሙን መንገድ ያቆራረጡበት እግሮቻቸው መንቀሳቀስ አቆሙ፡፡ ምኒልክ እንደ አንድ ሰው አሸለቡ፡፡ ሐዘን በቤተ መንግሥቱ ጥላውን አጠላ፡፡ መሪር ሐዘን ኾነ፡፡

ለዓመታት ከአባ ዳኛው ጋር ጎን ለጎን በዙፋን ላይ የተቀመጡት፣ እንደ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የትዳር አጋር ሆነው ምስጢር የተጋሩት፣ ዓድዋ ድረስ አብረው የተጓዙት፣ በዓድዋ ላይ ደማቅ ታሪክ የጻፉት እቴጌ ጣይቱ አብዝተው አለቀሱ፡፡ የእምዬ መሞት ለእሳቸው የተለዬ ነው፤ እኒያ ዘውድ ጭነው በኩራት የተመላለሱት፣ በፊት በኋላ፣ በግራ በቀኝ በታላቅ አጀብ የተንቀሳቀሱት ታላቅ ንጉሥ ድጋሜ እንደማይነሱ ሲያውቁ እንዴት አይዘኑ፣ እንዴት ሆድ አይባሳቸው? ልጃቸው ልዕልት ዘውዲቱ አምርረው አዘኑ፡፡

ተክለጻዲቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው ʺ ገናናው ንጉሠ ነገሥት በ1900 ዓ.ም የዠመራቸው በሽታ እየጸና ሄዶ በታኅሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የሸዋ ንጉሥ በኋላም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ሁሉ ክፉውን በክፉ ሳይኾን፣ ክፉውን በደግነት እየመለሱ፣ ጥፋትን ሁሉ በትዕግሥት እያሸነፉ፣ ሀገር የሚሰፋበትን፣ ልማት የሚዳብርበትን፣ ሕዝብ ረፍትና ሰላም የሚያገኝበትን፣ ከማሰብና ከመፈጸም አልተቆጠቡም፡፡ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል” ብለዋል፡፡
በባለቤታቸው መሞት ልባቸው የተነካው እቴጌ ጣይቱ እንዲህ ሲሉ ተቀኙ፡፡

ʺ ነጋሪት ማስመታት፣ እምቢልታ ማስነፋት ነበረ ሥራችን
ሰው መኾን አይቀርም ደረሰ ተራችን” እውነት ነው ሰው መኾን አይቀርም ተራቸው ደረሰ፡፡ እሳቸውም ሰውነት ያዛቸውና አለፉ፡፡ ኃያላን የሰገዱላቸው አሸለቡ፡፡
በእሳቸው ሀዘን ልባቸው የተነካው ልጃቸው የቀድሞዋ ልዕልት፣ የኋላዋ ንግሥት ዘውዲቱም በአባታቸው መሞት ተቀኝተዋል፡፡

ʺዘውደና ሕለተ ወርቅ ካባና ቀሚስ
ባለወርቅ መጣምር እያለ ፈረስ
ይመስለኝ ነበረ ይሄ የማይፈርስ ” ብለው ተቀኙ፡፡ አባትም፣ ንጉሥም፣ መኩሪያና መመኪያቸውን አጥተዋል፣ ግርማቸውን ተነጥቀዋል፣ ከሞገሳቸው ተለይተዋልና ሀዘናቸው ከባድ ኾነ፡፡

የሀገሬው ሰው የታላቁን ንጉሥ መሞት በሰማ ጊዜ አብዘቶ አዘነ፡፡ እርሱም ሙሾ እየደረደረ አለቀሰ፡፡ አዎን ዳኛቸውን ያክል ንጉሥ አጥቷልና አዘነ፡፡
ʺ ምኒልክ ተክላችን ወዴት ጠፋ ካገር፣
ሸዋ አዲስ አበባ ታይቶባቸው ነበር” ሲል የሀገሬው ሰው ተቀኘ፡፡ የታላቁ ንጉሥ መሞት ልብ ሰበረ፣ ከቤተ መንግሥቱ ተሻግሮ በሀገሬው ላይም አንዣበበ፣ አስለቀሰ፣ አሳዘነ፡፡ እሳቸው መልካሙን ሁሉ አድርገዋልና ሞተውም ይኖራሉ፣ አልፈውም ያኮራሉ፡፡ የሚያኮራ ታሪክ ሠርተዋልና ያኮራሉ፣ ታላቅ ታሪክ ሠርተዋልና ያስመካሉ፡፡ ታላቅ ሥራ የሠሩት ሲሞገሱ፣ ሲወደሱና ሲነሱ ይኖራሉ፡፡ ስማቸውን በደመቀው የታሪክ ብራና ላይ ያጽፋሉ፡፡ በዘመናቸው መልካሙን የሚያደርጉት ሁሉ በክብርና በዝና ይጠራሉ፡፡ ከፍ ከፍም ይላሉ፡፡ ስምን ገናና አድርጎ፣ በትውልድ ኹሉ ይወደዱ ዘንድ መልካሙን ሁሉ ያደርጉ፡፡ ንጉሥ ኾይ መልካም ረፍት፤

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሙስና የሥነ-ምግባር ዝቅጠት ውጤት ነው!”
Next articleኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍና ለደን መልሶ ልማት ላደረገችው አስተዋጽዖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አገኘች።