“ሙስና የሥነ-ምግባር ዝቅጠት ውጤት ነው!”

364

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምንም እንኳን ሙስና እንደሚፈጸምበት ሁኔታ የተለያዩ ብያኔዎች ቢሰጡትም ፤ ስለሙስና ትርጉም የሰጡ ምሁራን ሙስና ማለት በግል ወይም በቡድን፣ በመሪዎች ወይም በቢሮክራቶች ሥልጣንና ኀላፊነትን መከታ በማድረግ የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለግል ጥቅም የማዋል ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊት ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡

በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ስርቆት፣ ዝርፊያ እና ማጭበርበር መፈፀም፤ ሕግና ሥርዓትን በመጣስ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጎሰኝነት አድሎ መፈፀም፣ ፍትሕን ማጓደል እና ሥልጣንና ኀላፊነትን አላግባብ በመጠቀም ሕገወጥ ጥቅም ማግኛ ነውም ይሉታል–ሙስናን።

ብዙ ትርጓሜዎች ቢሰጡም ሙስና የሥነ-ምግባር ዝቅጠት ውጤት ማሳያ ነው፡፡ የሥነ-ምግባር ጉድለቱ የሞራል ንቅዘትን ወልዶ በሙስና ያስለክፋል። ይህ የሥነምግባር ዝቅጠት ውጤት ደግሞ ሕግና ሥርዓትን ማክበርና ማስከበር ባልቻሉ ሀገራት ላይ በርትቶ ይታያል፡፡

ዓለማቀፉ ኢኮኖሚክ ፎረም ቆየት ባለ መረጃው በዓለም በየዓመቱ 3 ነጥብ 6 ትሪሊየን ዶላር በሙስና ይመዘበራል፡፡

ደይሊ ኒውስ በቅርቡ ያስነበበው ዘገባም ቢኾን በዓለም ከ3 ትሪሊየን ዶላር በላይ በሙስና እንደሚመዘበር ነው የዘገበው፡፡

አፍሪካ ከዓለማችን በሙስና ክፉኛ ከተጎዱ አህጉራት መካከል ቀዳሚነቱን ትይዛለች፡፡
በትራነስፓራንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ መሰረት አፍሪካ በየዓመቱ 140 ቢሊየን ዶላር በሙስና እንደምታጣ አስታውቋል። በአፍሪካ 75 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ጉቦ ይከፍላሉ ሲልም አስነብቧል። ሁኔታውና ደረጃው ይለያይ እንጂ በሙስና ሰለባ ያልኾነ ዜጋ፣ ያልተፈተነ ሀገር የለም፡፡

ይህን ሀገር አንቃዥ በሽታ፣ ለመመከት በኢትዮጵያ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሲቋቋም የፀረ ሙስና ትግሉ ዓላማ ያደረገው ማስተማርን፣ መከላከልና ሕግ ማስከበርን ነው።ኾኖም አሁን ላይ ሙስና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ስጋት ኾነው ከተደቀኑ ችግሮች ተርታ ተሰልፏል፡፡ ከከፍተኛው ሙስና እስከ ዝቅተኛው የሙስና ሁኔታ ኢትዮጵያ ፈተና ላይ ናት።

በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሁሉ ያለምንም ምልጃ አገልግሎት ማግኘት ፈተና ኾኗል። መንግሥት ደመወዝ ይከፍላል አገልጋይ ግን ከተገልጋዩ እጅ ይመነትፋል፣ አደጋው ደግሞ ይህ ድርጊት እንደ ብልህነት፣ እንደ ብልጠት መታየቱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንዳሉት ሙስና ሳይሠሩ የሚበሉ ብቻ ሳይኾን የሚሠራን የሚበሉ ክፉ ሰዎችን ፈጥሯል፡፡ የገጠመውን ሀገራዊ ችግር እንደ እድል ተጠቅመው “ቀይ መስመር የተባለውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል” ነው ያሉት።
መንግሥትም ለችግሩ እልባት ለመስጠት የፀረ-ሙስና ዘመቻ ከፍቷል። ከሰሞኑም አዲስ የፀረ- ሙስና ብሔራዊ ኮሜቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ሥነ-መግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ- እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ሙስና አሳሳቢ ጀረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በኮሚሽኑ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም የተደራጀ ሌብነት ሥርዓትንና ተቋማትን እያፈረሰ፣ ግጭቶችን እየፈጠረ፣ ከግጭት አትራፊዎችን እየፈጠረ ነው ተብሏል። በዚህም ሙስና በሀገሪቱ ብሔራዊ ስጋት ኾኗል።

ሙስና ሕዝብ እያማረረ፣ የመንግሥትን ሚናና እምነት እየሸረሸረ፣ ሀገር እየበደለ ነው። ዘመቻው በሙስና የፈረሱ ተቋማትን መልሶ የሚያደራጅ፣ በቅንጅት ለመታገል አቅም የሚፈጥር፣ የሕዝባዊ አጋርነትን የሚያነቃቃ ይኾናል ብለውታል።

ጉዳዩ በሙስና ጉዳዮችን የሚያስፈጽሙና የሚፈጽሙ “ጉዳይ ገዳዮች” ባሉበት ሁኔታ በሙስና ሰለባ ያልነ የለምና የሙስና ድርጊትን ማውገዝ፤ መከላከልና ማጋለጥ የሁሉንም ኀብረተሰብ ኀላፊነት የሚጠይቅ ይኾናል፡፡

የፍትሕ ተቋማትና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናን የሚዋጋ ማኅበረሰብን መፍጠርም ይኖርባቸዋል፡፡

ሙስና ሕገወጥ በኾነ መንገድ ጥቂቶችን ተጠቃሚ፤ ሰፊውን ሕዝብ ደግሞ ለጉስቁልና የሚዳርግ፣ የልማት ሥራዎችን የሚያደናቅፍ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚጎዳ፣ ፍትሕን የሚያዛባ፣ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት እንዲቀንስ የሚያደርግ ወንጀል በመኾኑ መፍትሔ ፍለጋው ላይ በቁርጠኝነት ርብርብ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡

የሙስና ድርጊትን መከላከል የነቀዘ አስተሳሰብን፣ የዘቀጠ ሥነ-ምግባርንና ሞራልን ማረም፣ ሌብነትን መዋጋት መኾኑን መገንዘብ የግድ ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜን ጨምሮ በአራት ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።
Next articleʺሞተውም ይኖራሉ፣ አልፈውም ያኮራሉ”