
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜን ጨምሮ በአራት ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስም 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ከሁለት ፋብሪካዎች ገዝተው ለግለሰቦች በመሸጥ፤ ከ30 ሚሊዬን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ የአገልግሎቱ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተርን ጨምሮ በአራት ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ እንደመሰረተባቸው ተገልጿል፡፡
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾች በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ውስጥ 1ኛ ተስፋዬ ደሜ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር፣ 2ኛ አሸናፊ ተስፋዬ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ዋና ክፍል ሃላፊ፣ 3ኛ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 4ኛ ተከሳሽ ሙስጠፋ ሙሳ የግዢ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸው ተጠቅሷል፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ተገቢ ያልሆ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2013 እና 2014 ዓ.ም በተለያዩ ወራት በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምንም አይንት ሲሚንቶ ግዢ ባልተፈፀመበት ሁኔታ በስሙ ሲሚንቶ ከፋብሪካዎች በአነስተኛ ዋጋ በመግዛትና ገበያ ላይ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ህገ-ወጥ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በመስሪያ ቤቱ ስም ግዢ እንዲፈፀም እና ሲሚንቶው ወደ መስሪያ ቤቱ ገቢ ሳይደረግ አየር ላይ ተሸጦ ለግል ጥቅሙ እንዲውል አድርገዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ተገልጿል፡፡
ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ምንም አይነት የግዢ ፍላጎት ሳይኖር በአገልግሎቱ ስም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድምሩ 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመግዛት ወደ ተቋሙ ገቢ ሳያደርጉ ገበያ ላይ በመሸጥ 30 ሚሊዮን 99 ሺ 360 ብር ጥቅም ያገኙ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል ሲል ከፍትህ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ደርሷቸው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን ተከሳሾችም የክስ መቃወሚያ ካላቸው በጽሁፍ እንዲያቀርቡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎትም ለታህሳስ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!