
ደሴ፡ ታህሳስ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ለ31ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ” ሴቶችን አከብራለሁ ፤ ጥቃታቸውንም እከላከላለሁ” በሚል መሪ መልእክት “የነጭ ሪቫን ቀን” ማጠቃለያ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ የመዝጊያ ዝግጅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና በጤና ሚኒስቴር የሴቶች ህፃናት ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ፋጡማ ሰይድ ተገኝተዋል።
በደሴ ከተማ የጾታ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንድ ማእከል አገልግሎት አስተባባሪ ሲስተር መዲና ወርቅነህ ከ 2012 ወዲህ በምሥራቅ አማራ 1385 አዋቂ እና ህፃናት መደፈራቸውን ገልፀዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነትም የጾታዊ ጥቃት ባለፋት ሁለት ዓመታት ቁጥሩ መጨመሩን ያነሱት አስተባባሪዋ ተጎጅዎችን ባለን አቅም ማስተናገድ የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል።
የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሕይወቴ ስማቸው ጾታዊ ጥቃትን ለማስቆም ሁላችንም በየእለት ተእለት ኑራችን ላይ ዋና ጉዳይ ልናደርገው ይገባል ነው ያሉት። ድርጅታቸውም እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ፣ ማኅበራዊ ፣ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ•ር ቤተልሔም ላቀው የሴቶች ጥቃትን ለመከላከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሕጎችን በማሻሻል በወንጀለኞች ላይ እርምጃውን ማጠናከር አለበት ነው ያሉት።
የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የሴቶች ጥቃትን መከላከል ከምንም ነገር በላይ ተግባርን የሚጠይቅና ድርጊቱን ለማስቀረት አስተሳሰብ ላይ መሠራት አለበት ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ፋጡማ ሰይድ ጾታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ድርጊቱን ለማስቆም ሁሉም ማኅበረሰብ መረባረብ ይገባዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!