ሙስናን መታገል ከአስተሳሰብ ይጀምራል” ምክትል ኮሚሽነር ማሩ ቸኮል

100

ባሕር ዳር: ሕዳር 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሌብነት እና ብልሹ አሠራር መሰረታዊ ፈተናዎች የሆኑባት ኢትዮጵያ መጻዒ እጣ ፋንታዋ አጣብቂኝ ውስጥ የወደቀ ይመስላል፡፡ በአቋራጭ መጠቀም፣ ሰርቆ መሰብሰብ እና ከድሆች ጉሮሮ መመንተፍ በየትኛውም ደረጃ የሚስተዋል የአሠራር ባህል ከመሰለ ውሎ አድሯል፡፡

 

አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በውስጣቸው የተሰገሰገው ደላላ የተገልጋዮች ምሬት ስለመሆኑ በየአደባባዩ የሚሰማ ብሶት ሆኗል፡፡ ያለእጅ መንሻ አገልግሎት መስጠት ነውር በመሰለበት የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሰጭዎችም ተቀባዮችም የችግሩ ባለቤቶች ናቸው፡፡

 

የችግሩን መኖር እያወቁ “የዝሆን ጆሮ ይስጠን” ያሉት የተቋማቱ የሥራ ኅላፊዎች እና ባለሙያዎች ኅላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ስለማይጠየቁ ተገልጋዮች ለማን አቤት ማለት እንዳለባቸው እስኪጠፋቸው ድረስ ችግሩ ሥር ሰድዷል የሚሉት ብዙ ናቸው፡፡ ችግሩ በሥርዓቱ ተስፋ ከማጣት አልፎ የሀገር ሕልውና አደጋም ሆኗል፡፡

 

ስርቆት እና ሌብነት ከሕዝብ በወጡ የማሕበረሰቡ አባላት የሚፈጸም አስነዋሪ ድርጊት ነው ያሉን የአማራ ክልል ፀረ-ሙስና እና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ማሩ ቸኮል ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው ስርቆት እና ሌብነት የኢትዮጵያዊያን መገለጫ እሴት አልነበረም የሚሉት ምክትል ኮሚሽነር ማሩ ከሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎ ጎን ለጎን ስለችግሩ አሳሳቢነት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

 

የፀረ- ሙስና ትግሉ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ማረም እና የተመዘበረ የሕዝብ ሃብትን ማስመለስ ላይ የሚያተኩር ሂደት ነው፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ ማሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመሻገር የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡

 

“ሙስናን መታገል ከአስተሳሰብ ይጀምራል” የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የሥነ-ምግባር ትምህርቱ ከፀረ-ሙስና ትግሉ እኩል ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ መገንባት የጋራ ጥረትን ይጠይቃል ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ማሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና የሲቪክ ማሕበራት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

 

ብልሹ አሰራርን መታገል እና ሌብነትን ማስቆም ለአንድ ተቋም የሚተው ተግባር አይደለም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ሕዝብ ጥቆማ እና መረጃ በመስጠት ከፍትሕ እና የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች ከተቋቋሙ የሥነ-ምግባር ክበባት ጋር በጋራ መስራት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተማሪዎች ጋር ተቀራርቦ መነጋገር የኮሚሽኑ የቀጣይ ጊዜያት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ምክትል ኮሚሽኑ ተናግረዋል፡፡

 

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

 

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq

በዌብሳይት amharaweb.com

በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

ትዊተር https://bit.ly/336LQaS

ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO

አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport

አሚኮ መረጃ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous article“ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ሚናዋን ትወጣለች” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Next articleየአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ሜካናይዜሽንን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን ተረከበ።