የክዋኔ ኦዲት ግኝት የፀረ-ሙስና ትግሉ ሁነኛ ማስረጃ እና መረጃ መኾኑን ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ፡፡ 

237

ባሕር ዳር: ሕዳር 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚቀርቡ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ለፀረ-ሙስና ትግሉ ሁነኛ ማስረጃ እና መረጃ ኾነው እንደሚያገለግሉ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታውቋል፡፡

 

በክልሉ የሚስተዋለው የሙስና ወንጀል ምርመራ ተለምዷዊ የሚባል ነው፡፡ የሙስና ወንጀል የመንግሥት እና የልማት ተቋማትን የአሠራር ሂደት በሚገባ በሚያውቁ አካላት የሚፈጸም ስርቆት በመኾኑ ምርመራው ውስብስብ እና ፈታኝ ሲኾን ይስተዋላል፡፡

 

በመንግሥት ተቋማት እና የልማት ድርጅቶች የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን እና ሌብነትን ለመከላከል የተሻለ የምርመራ አቅምን ማሳደግ የግድ ይላል ያሉን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ ዝግያለ ገበየሁ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዘወተረ የመጣው የክዋኔ ኦዲት ግኝት የፀረ-ሙስና ትግሉ ሁነኛ ማስረጃ እና መረጃ እንደኾነም አቶ ዝጋለ ጠቁመዋል፡፡

 

የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ሕጋዊ መልክ ያለውን እና ወረቀት ላይ የሰፈረውን የፋይናንስ ወጭ ሪፖርት ተግባር ላይ መዋል አለመዋሉን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ስለሚያሳዩ ለፀረ-ሙስና ትግሉ ጠቃሚ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል ምክትል ቢሮ ኅላፊው፡፡

 

በቅርቡ በአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ የቀረቡትን የክዋኔ ኦዲት ግኝት ሪፖርቶች እንደተመለከቷቸው የገለጹት አቶ ዝጋለ የአንዳንዶቹ ምርመራዎች የመረጃ ምንጭ ፍትሕ ቢሮ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ የሚልካቸውን የኦዲት ግኝት ሪፖርት መሰረት አድርገው ተጨማሪ ምርመራ እና በሕግ መቅረብ ያለባቸውን ተጠርጣሪዎች ለማቅረብ እንደሚሠሩም አቶ ዝጋለ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

 

በከተማ አስተዳደሮች፣ በገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ፣ በክልሉ ጤና ቢሮ እና በገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ የቀረቡ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶችን መሰረት በማድረግ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግም ምክትል ቢሮ ኅላፊው ጠቁመዋል፡፡

 

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የምርመራ ዘገባ በሠራባቸው የመሬት ማዳበሪያ ምዝበራ እና ማጭበርበር ተጠርጣሪዎች ላይ ፍትሕ ቢሮ ምርመራ ከፍቶ እየሠራ መኾኑን የጠቆሙት አቶ ዝጋለ የተመዘበረውን ገንዘብ የማስመለስ እና ተጠርጣሪዎችንም በሕግ የመጠየቅ ሥራም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

 

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

 

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq

በዌብሳይት amharaweb.com

በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

ትዊተር https://bit.ly/336LQaS

ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO

አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport

አሚኮ መረጃ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous articleአሸባሪው የሸኔ ቡድን በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝና መንግሥት ሕግን እንደሚያስከብር የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አስታወቁ፡፡
Next articleʺኢትዮጵያ ብዝኃነቷ ለአንድነቷ ብርታት፣ አንድነቷ ለብዝኃነቷ ጉልበት የኾኗት ሕብረ ብሔራዊት ሀገር ናት” የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር