
ባሕር ዳር: ሕዳር 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሐዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው። በዓሉ “ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተከበረ የሚገኘው። በክብረ በዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፊዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የሁላችን ቤት ናት ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋራ የምናድግበት በጋራ የምንበለጽግበትን፣ በጋራ በሰላም የምንኖርበትን ሁኔታ መፍጠር ካልቻልን ማናችንም መኖር መበልጸግ፣ በሰላም ወጥተን መግባት አንችልም ነው ያሉት።
የእያንዳንዳችን ችግር ሊፈታ የሚችለው ቅድሚያ የኢትዮጵያ ችግር ሲፈታ ብቸቻ ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ በመልዕክታቸው። “ሀገር በቤት ይመሰላል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ማገሩ፣ ወራጁ፣ ቋሚውና ጣራው ተዳምረው ቤት እንደሚኾኑ ኹሉ ሁሉም ብሔሮች፣ ሁሉም ዜጎች፣ ሁሉም ባሕሎች ተዳምረው ሰበዝ ኾነው ሲደመሩ ነው ውቢቷን ኢትዮጵያ የሚያሳዩት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት “በተናጠል ጎልተን ለመታየት ሳይኾን በጋራ ለማበብ ልባችን የቀናና አዕምሯችን የሚያስታውል እንዲኾን ላሳስባችሁ እወዳለሁ” ነው ያሉት።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ከትናንትና መላቀቅ ያልቻሉ ዋልታ ረገጥ መገፋፋትን የሚመርጡ፣ በራሳቸው ሳይኾን በጠላት አጀንዳ የሚመሩ፣ በንጹሐን ደም የፖለቲካ አጀንዳ የሚሠሩ እኩያን ቡድኖችና ግለሰቦች አሉ፤ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ግን አይችሉም” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“መልካም ልጆቻችንን ለመገንባት፣ መጪው ትውልድ ከልመና የተገላገለ፣ ሰርቶ የሚበላ፣ ጎረቤቱን የሚወድ በጋራ እሤቱ የሚኮራ እንዲኾን መገፋፋቱንና መጠላላቱን ተወት እንድናደርገው አደራ እላለሁ” ነው ያሉት።
የተሸናፊዎች ዓላማ ንጽሐንን ማጎሳቆል መግደል ነው፣ ኢትዮጵያን ለመናጥ አርፈው ለማይተኙት ጀሮ አትስጡ ከመንግሥት ጋር በትብብር፣ በሕግ፣ በአንድነት ሰላማችን ማስከበር እንድንችል የበኩላችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ምንም ጨለማ የሚመስሉ ነገሮች ቢታዩም
ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት ከልባችሁ እንድትሠሩ አደራ እላለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ መረጃ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck