ʺኢትዮጵያ ብዝኃነቷ ለአንድነቷ ብርታት፣ አንድነቷ ለብዝኃነቷ ጉልበት የኾኗት ሕብረ ብሔራዊት ሀገር ናት” የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

163

ባሕር ዳር: ሕዳር 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሐዋሳ ከተማ ተከብሯል፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

 

በበዓሉ መልእክት ያስተላለፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበር ዓላማው የሕዝብን አንድነት ለማጠናከር በማሰብ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ያለውን እና ወደፊት የሚተካውን ትውልድ አንድነት እና ትሥሥር ለማጎልበት እና ብሔር ብሔረሰቦች ባሕላቸውን እየተለዋወጡ፣ ዴሞክራሲን እያጎለበቱ ለዘላቂ ሰላም በአንድነት እና በአብሮነት እንዲሰለፉ ለማስቻል መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

 

የበዓሉ ዓላማ እንዲሳካ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዓሉን በልዩ ልዩ ዝግጅት ሲያከብር መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡ የበዓሉ መከበር በሕዝቦች መካከል መከባበር እና መተዋወቅ እንዲኖር አስተዋጽዖ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሕብረ ቀለማት ያሸበረቀች፣ የባለ ብዙ ማንነት ባለቤት ለመኾኗ ማረጋገጫም ኾኗታል ነው ያሉት፡፡

 

የብሔር ብሔረሰቦች አምባሳደሮች በበዓላቱ የሚያቀርቧቸው ጭፈራዎች፣ የሚዋቡበት መዋቢያ፣ አልባሳቱ እና ዜማቸው ተጫማሪ ጌጥ ኾኗልም ነው ያሉት፡፡

 

በዓሉ የሚሰጣቸውን ጥቅሞች በመረዳት አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ኢትዮጵያ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ከፍ እንድትል እንደሚደርጋትም ተናግረዋል፡፡ በዓሉ በሕዝቦች ዘንድ አንድነት እና መከባበርን እንደሚገነባም ገልጸዋል፡፡ መቀራረብና መተማመን ይፈጥራልም ነው ያሉት፡፡

አንድነቷ የተጠናከረ እና ሰላሟ የተጠበቀ ሀገር እንድትኖር እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማምጣት በማሰብ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

 

ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በሰላም መፍታት የሚችሉ መኾናቸውን ባሳዩበትና ታላቅነታቸውን ለዓለም ባስመሰከሩበት ማግሥት የሚከበር በዓል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባእዳን ሊጭኑባት ባሰቡት የራስ ያልኾነ ማንነት ያልተንበረከከች፣ ለብዙ ዘመናት በራሷ የአስተዳደር ቅርጽ የመጣች፣ ብዝኃ ማንነቶቿን ከሀገራዊ አንድነት ጋር አስተሳስራና አዋህዳ የቆዬች፣ ብዝኃነቷ ለአንድነቷ ብርታት፣ አንድነቷ ለብዝኃነቷ ጉልበት የኾኗት ሕብረ ብሔረዊት ሀገር ናትም ብለዋል አፈ ጉባዔው፡፡

 

የጋራ ቤታችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም አንድነቷ ምሰሶ፣ ብዝኃነቷ ደግሞ ለአንድነቷ ደጋፊ ወጋግራ ኾነው አገልግለዋል ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፡፡

 

ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ እንዲከበር የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ አሻራቸውን አስቀምጠዋልም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተተገበረው ፌዴራሊዝም ዜጎችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ቢያጎናጽፍም፣ ከአተገባበሩ ጋር ተያይዞ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ገንብተናል ለማለት አንደፍርም ነው ያሉት፡፡

 

ለሀገረ ግንባታ የሚያግዙ የጋራ እሴቶችን ለማጠናከር፣ ብዝኃነትን ያከበረ አንድነትን ከማጽናት እና ከማክበር አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በሕዝቦች ዘንድ ከመተማመን ይልቅ መጠራጠር እንዲኖር ሐሰተኛ ትርክቶችን ፈብርኮ በማሰራጨት በሀገር ላይ ጸንቶ የኖረውን የሰላም እሴት በመሸርሸር ዋጋ አስከፍሎናልም ነው ያሉት፡፡

 

የሀሰት ትርክቱ በየቦታው ለሚነሱ ግጭቶች ማቀጣጠያ ባሩድ ኾኖ እያገለገለገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ፌዴራሊዝም ሥርዓት መጠቀም ለልዩነቶች ምክንያት ሊኾን እንደማይችልም አንስተዋል፡፡ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለመተግበር በሚደረገው ሂደት በሚፈጸመው ስሕተት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ያልተፈቱ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑንም አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል፡፡

 

ዜጎች በማንነታቸው እንዲገደሉ እያደረገ ያለው በአለፉት ዓመታት በታሪካዊ ጠላቶች እና በተላላኪዎች በተዘራው ጥላቻ ምክንያት ነውም ብለዋል፡፡ ዜጎችን በማንነታቸው ነጥሎ መግደል አንድነትን በመሸርሸር ኢትዮጵያን የማፍረስ ፕሮጄክት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በማንነታቸው ብቻ የሚገደሉ ንጹሐንን ለመታደግ መፍትሔው አንድነት ነውም ብለዋል፡፡

መንግሥት የጀመረውን የሕግ የበላይነት ማስከበር አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ለሕግ የበላይነት መከበርና ለሀገር አንድነት መጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ የቆመችው በሕዝቦቿ ጥረትና መስዋዕትነት ነው ያሉት አቶ አገኘሁ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠበቅና የሀገርን ደኅንነት ማረጋገጥ የምርጫ ጉዳይ አይደለምም ብለዋል፡፡ አንዳችን ያለ ሌላው ድጋፍ ልንኖርና ልንበለጽግ፣ ሰላማችን ሊከበር አይችልም ነው ያሉት፡፡ በዓሉ በስኬት እንዲዘጋጅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡

 

በታርቆ ክንዴ

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

 

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq

በዌብሳይት amharaweb.com

በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

ትዊተር https://bit.ly/336LQaS

ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO

አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport

አሚኮ መረጃ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous articleየክዋኔ ኦዲት ግኝት የፀረ-ሙስና ትግሉ ሁነኛ ማስረጃ እና መረጃ መኾኑን ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ፡፡ 
Next article“ኢትዮጵያ ውስጥ ከትናንትና መላቀቅ ያልቻሉ ዋልታ ረገጥ መገፋፋትን የሚመርጡ፣ በራሳቸው ሳይኾን በጠላት አጀንዳ የሚመሩ፣ በንጹሐን ደም የፖለቲካ አጀንዳ የሚሠሩ እኩያን ቡድኖችና ግለሰቦች አሉ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)