
አዲስ አበባ: ሕዳር 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ በንፁሃን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በተመለከተ እናት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ፓርቲ (ኢ.ሕ.አ.ፓ) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ.ኢ.አ.ድ) የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላለፉት አራት ዓመታት በወለጋ በአማራዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል። በባለፈው አራት ዓመታት የጥቃቱ ሰለባዎች በዋናነት አማራዎች ይሁኑ አንጂ ኦነግ ሸኔን የሚቃወሙ የኦሮሞ ተወላጆችም የችግሩ ሰለባ ኾነዋል ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ መንግሥት የንፁሃንን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆምና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሁነው አሸባሪ ቡድኑን በሚደግፉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ፣ መዋቅሩን እንዲያጠራና በጥፋተኞች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት።
ፓርቲዎቹ በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ሚዲያዎችና የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት ጭፍጨፋው መቋጫ እንዲያገኝ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።
ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ አካባቢው በኮማንድ ፖስት እንዲመራም ጠይቀዋል።
የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ በዚህ ግጭት የተሳተፉ ሁሉ በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!