ትኩረት የሚሹት የተጓተቱ የመሥኖ ፕሮጀክቶች።

138

ባሕር ዳር: ሕዳር 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በመጓተት ላይ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ የመሥኖ ፕሮጀክቶችን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ እየሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል መሥኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ገልጿል። የቢሮው ምክትል ኀላፊ አየልኝ መሳፍንት እንዳሉት በአማራ ክልል 30 ሺህ 965 ሄክታር መሬት የሚያለሙና 61 ሺህ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ሚችሉ 249 አነስተኛና መካከለኛ የመሥኖ ፕሮጀክቶችን ይገነባሉ።

ከዚህ ውስጥ 160 ፕሮጀክቶች በኮሮና ወረርሽኝ፣ በካሳ ክፍያ፣ በግንባታ እቃዎች ላይ በተፈጠረ የዋጋ ልዩነት፣በሌሎችም ማኅበረሰባዊ ችግሮች ምክንያት በተቀመጠላቸው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ሲኾን 89 የሚጠጉት ፕሮጀክቶች ደግሞ በአዲስ የሚገነቡ ናቸው።

በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ ከፍተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችም በተቀመጠላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅ ችግር መኖሩን ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እንደ መገጭ፣ ታችኛውና ላይኛው ርብ፣ አጅማ ጫጫና ጣና በለስ ይገኙበታል። በተለይም ደግሞ መገጭና ታችኛው ርብ መስኖ ግድቦች ለረጅም ዓመታት መጓተታቸውን ነው ኀላፊው ያነሱት። ፕሮጀክቶቹ 33 ሺህ 450 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉና 66 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ችግሮን ለመፍታት ምን የመፍትሔ አቅጣጫ ተቀምጧል?

👉 ከዚህ በፊት በተለያየ አቅጣጫ ይከናወን የነበረውን የካናልና የግድብ ሥራ በማስቀረት የካናል ሥራው ከግድቡ ጀምሮ እንዲሠራ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ይህም ካናሎች በደረሱበት እንዲያለሙ ያስችላል።

👉ሙሉ በሙሉም ኾነ በከፊል አገልግሎት በመሥጠት ላይ የሚገኙ የመሥኖ ካናሎች የጽዳት ሥራም እየተሠራ ይገኛል፡፡

👉በኮሮናና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማካካስ ፕሮጀክቶቹ የጠየቁት ማሻሻያ ተሰልቶ ለገንዘብ ቢሮ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

👉የሚከሰቱ የቴክኒክና ማኅበራዊ ችግሮች ከአቅም በላይ በሚኾኑበት ጊዜ ደግሞ ለክልሉ የሥንዴና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ በማቅረብ እንዲፈታ የሚያደርጉ የግንባታ ክትትል ባለሙያዎች መመደቡን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ በፕሮጀክቶች ላይ ማኅበራዊ ችግር ሲያጋጥም፣ ዲዛይን ክለሳ መደረግ ሲያስፈልግ፣ ተሰርተው ርክክብ ሳይደረግባቸው የፈረሱ ካሉ እንዲሠሩ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

👉በቀጣይም ፕሮጀክቶች ላይ የሚነሱ ችግሮችን በመከታተል መፍትሔ የሚሠጡ፣ ችግሩ ከአቅማቸው በላይ ሲኾን ደግሞ ለሚመለከተው አካል የሚያቀርቡ ከአርሶ አደሮች የተውጣጣ የመሥኖ ውኃ ተጠቃሚዎች ማኅበራት ይቋቋማል፡፡

👉በስሚንቶ እጥረት የቆሙ ግድቦች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ለፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

👉የአካባቢው ማኅበረሰብም የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላም በመፍታት ኮንትራክተሮች ሥራዎችን በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲያጠናቅቁ ድጋፍ ማድርግ እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ መረጃ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous articleበኩር ጋዜጣ – ሕዳር 26/2015 ዓ.ም ዕትም
Next articleየግብርና ዘርፉን ለማዘመን መንግሥት የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ መኾኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡