
ባሕር ዳር: ሕዳር 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባንኮች የግብርና ሥራን ለማዘመን የሚያግዙ ማሽኖችን መግዛት ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች የተሳለጠ ብድር ማቅረብ እንዳለባቸው ተገልጿል። ይኽ የተባለው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በግብርና ሜካናይዜሽን ዙሪያ ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በውይይቱ ላይ የግብርና ባለሙያዎች፣ የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽን አቅራቢ ድርጅቶች እና የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው። በመድረኩ ላይ በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ እና አርሶ አደሮች ዘመናዊ የእርሻ ማሽኖች ባለቤት እንዲኾኑ ሁሉም መረባረብ እንደሚገባው ተጠቅሷል። ማሽን አቅራቢ የንግድ ድርጅቶች ጥራት ያለው የእርሻ ማሽን እንዲያስገቡ ተጠይቋል። ለማሽኑ የሚኾን በቂ መለዋወጫ እቃዎችን እና የጥገና ማዕከል እንዲያቋቁሙ እንዲሁም ለአርሶ አደሮች ሥልጠና ሊሰጡ እንደሚገባም ተገልጿል።
የእርሻ ትራክተሮች እንዲሁም የማጨጃና መውቂያ ማሽኖች የቀረቡ ቢኾንም ወደ አርሶ አደሮች የሚተላለፋበት ሂደት ግን ውጣ ውረድ የበዛው እና የተጠቃሚዎችን ሁኔታ ያላገናዘበ መኾኑ ተገልጿል። ለአብነትም በፀደይ ባንክ በኩል ለአርሶ አደሮች ትራክተር በሚተላለፍበት ጊዜ ሊብሬውን እንደዋስትና መያዝ ሲገባ የቤት ካርታ እንደተጨማሪ ዋስትና እንዲያስይዙ መጠየቅ አግባብ እንዳልኾነ ነው የተብራራው። በገጠር ውስጥ የሚኖርን አርሶ አደር የከተማ ቤት ካርታ እንዲያስይዝ መጠየቅ ተገቢ አለመኾኑም ተጠቁሟል። የብድር መመለሻ ጊዜው ያጠረ እና የአርሶ አደሮችን አቅም ያላገናዘበ መኾኑም በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መኾኑ ተገልጿል።
የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ በዘመናዊ መልኩ መከናወን እንዲችል ባንኮች የሜካናይዜሽን ማሽኖችን ለሚገዙ አርሶ አደሮች ተገቢውን ብድር ማመቻቸት እንዳለባቸው ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ብድር ባልተመቻቸበት ሁኔታ በአርሶ አደሮች አቅም ብቻ ማሽን ሊገዛ እና ግብርናው ዘምኖ ለሀገር ኢኮኖሚ ደጋፊ ሊኾን እንደማይችልም ነው የተብራራው።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተወካይ ተሳታፊ አቶ አንማው ገዳሙ ልማት ባንክ ዋና ዓላማው አርሶ አደሩ ማልማት እንዲችል ማገዝ ነው ብለዋል። ብድር ለመስጠት የሚጠየቀው ወለድም 11 ነጥብ 5 በመቶ ስለመኾኑ ገልጸዋል። ብድር በሚሰጥበት ወቅትም የትራክተሩን ሊብሬ ብቻ እንይዛለን ብለዋል። ማሽኑ ተንቀሳቅሶ የሚሠራበትን አካባቢ ለባንኩ እንዲያሳውቅም ይደረጋል ነው ያሉት። አርሶ አደሩን ወደ አላስፈላጊ እንግልት በማስገባት ከብድር የሚያርቅ እና የግብርናውን ሜካናይዜሽን የሚጎዳ የተጋነነ ዋስትና አንጠይቅም ብለዋል። ከባንኩ የበላይ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመነጋገር ኅብረተሰቡን ከዚህም በላይ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የአባይ ባንክ ተወካይ ተሳታፊው አቶ ሲሳይ ጸጋየ በበኩላቸው ባንኩ ከግብርና ቢሮ ጋር በነበረው ውይይት ለአርሶ አደሮች የሚሰጠውን አገልግሎት አሻሽሏል ብለዋል። በዋስትና በኩል ለተነሳው ጉዳይ መልስ ሲሰጡም ባንኩ አርሶ አደሮችን ተጨማሪ ዋስትና ከመጠየቅ ተቆጥቦ አሁን ላይ የማሽኑን ሊብሬ ብቻ በዋስትናነት የመያዝ አሠራር ማበጀቱን ጠቅሰዋል።
የጸደይ ባንክ ተወካይ ተሳታፊው አቶ ይርጋ ጌትነት “ትራክተሩን በማንቆጣጠርበት ኹኔታ በሊብሬው ብቻ ዋስትናነት ብድር ለመስጠት እንቸገራለን” ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!