በኮምቦልቻ ከተማ እስከ አምስት ኮከብ የሚኖራቸው ስድስት ሆቴሎች ሊገነቡ ነው፡፡

439

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ባለመገንባታቸው ከተማዋ ከዘርፉ ተጠቃሚ አለመሆኗን ባለሀብቶች ተናግረዋል፡፡

ኮምቦልቻ በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፍሰት በብዛት የሚገኝባት የደረቅ ወደብ ከተማ ናት። ከመደበኛ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አገልግሎት በተጨማሪ የአውሮፕላን ማረፊያ እና የኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር ጣቢያ መገኛም ናት፡፡ በከተማዋ ባሉት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምክንያትም ከነዋሪዎቿ ባለፈ የውጭ ሀገራት እና የሀገር ውስጥ ሰራተኞች እንዲሁም የባለሀብቶች መዳረሻ ሆናለች፡፡ ከተማዋ ለአፋር፣ ለምስራቅ አማራ አካባቢ እና ለትግራይ ክልል መተላለፊያ መንገድ በመሆኗ የበርካታ ተጓዦች ማረፊያም ናት፡፡

ወደ አክሱም፣ ግሸን ማርያም፣ አፋር ክልል ባሉ የጎብኝዎች መዳረሻዎችና ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚጓዙ የውጭ የሀገራትና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም ያርፉባታል። በኮምቦልቻ ከፍተኛ የሰዎች ፍሰት ይኑር እንጂ ሲደክም የሚያርፉባቸው፣ ምግብና መጠጦችንም የሚያገኙባቸው፣ ከተማዋን እና የሕዝቡን ቁጥር የሚመጥኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የሏትም። በመሆኑም በርካታ እንግዶች ወደ ሌላ ቦታ አልፈው ይሄዳሉ። ሆቴሎች ቱሪስት መጥን ባለመሆናቸውም ጎብኝዎችና ተጓዦች የኮምቦልቻ ቆይታቸውን ያሳጥራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት እየጎዳ ይገኛል፡፡

በከተማዋ በሆቴል ከተሰማሩት መካከል አቶ ሁሴን መሐመድ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በዘርፉ ሥራ እንደጀመሩ ተናግረዋል። ወደ ሥራው ሲገቡም ምግብ ቤት፣ መዋኛ ገንዳ፣ የመኝታ ክፍሎች፣ የመኪና ማቆሚያ ያለው ሆቴል ለመገንባት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውል በመያዝ እንደነበር ነው አቶ መሐመድ የተናገሩት። “ከተማ አስተዳድሩ ቃል የገባውን ቦታ ሙሉ ለሙሉ ባለመስጠቱ የመኝታ አገልግሎት ብቻ እንድንሰጥ ተገድደናል” ብለዋል አቶ ሁሴን። ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አለመኖር ደግሞ ከተማዋ በእንግዶች ተመራጭ እንዳትሆን አድርጓታል ነው ያሉት፡፡

በተሰጣቸው ቦታ ቦታ ላይ የምግብ ቤት አገልግሎት ለመስጠት ያደረጉት ጥረትም በቦታ እጥረት ምክንያት የሆቴሉን ፍሳሽ በየጊዜው ማስወገድ ስላልተቻለ ሥራውን እንዳቆሙትም ተናግረዋል። ቃል የተገባላቸው ቦታ ቢሰጣቸው በቶሎ ወደ ተሟላ ሥራ እንደሚገቡም ነው የተናገሩት፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳድር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባይነህ አበባው ችግሩ መኖሩን አምነው በከተማ አስተዳድሩ 32 የሚሆኑ ባለሀብቶች ቦታ ወስደው በሆቴል ኢንቨስትመንት እንደተሰማሩ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አስሩ በቅድመ ግንባታ ላይ፣ 12 ባለሀብቶች ደግሞ ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባታ ላይ ናቸው ብለዋል። በከተማዋ 32 ባለሀብቶች በሆቴል ኢንቨስትመንት ላይ ይሰማሩ እንጂ አሁን ላይ ደረጃውን ያሉት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ግን ከሦስት እንደማይበልጡ ነው አቶ አባይነህ የገለጹት፡፡

የሆቴል አገልግሎት ችግሩን ለመፍታት በክልሉ መንግስት ፈቃድ ተሰጥቶ ስድስት ደረጃውን የጠበቁ ሆቴሎችን ለማሰራት ዝግጅት እንደተጀመረም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ መንግስት በልዩ ሁኔታ የተፈቀዱት ስድስቱ ሆቴሎች ደረጃቸው እስከ ባለ አምስት ኮኮብ እንደሚሆኑም የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል። ከተማዋን ማሳደግና ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ባለሀብቶችን ወደ ከተማዋ ለማምጣት እየተሠራ እንደሆነም ነው አቶ አባይነህ የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

Previous articleግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ልዩነት በውይይት ለመፍታት ተስማማች፡፡
Next articleብዙ ቋንቋ ይወራበታል፤ ሳይግባባ የተመለሰ ግን የለም። እኔም ለሥራ ወደ ስፍራው ስቀርብ ለሥራ የያዝኳቸውን ዕቃዎች እንድሸጥ ተጠይቄ ነበር።