መንግሥት በአፋጣኝ የመከላካያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ በመላክ ህይወታቸውን እንዲታደግ በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ ያና ወረዳ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ተናገሩ።

786

ባሕር ዳር: ሕዳር 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ያና ወረዳ አንገር ጉትን ከተማ ከንጋቱ 11፡30 ስዓት ጀምሮ በንጹሃን ዜጎች ላይ ተኩስ ተከፍቷል፡፡ አሚኮ በስልክ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጭዎች “መንግሥት በአፋጣኝ የመከላካያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ በመላክ ህይወታቸውን እንዲታደግ ተማጽነዋል፡፡

ትናንት ምሽት 11 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ከወደ ነቀምት በሰባት ከባድ ተሸከርካሪዎች የታጠቁ ኃይሎች ወደ ከተማዋ እየገቡ ነበር ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ ዛሬ ከንጋቱ 11፡30 ስዓት ጀምሮ በከተማዋ ተኩስ መከፈቱን ነግረውናል፡፡ በዚህም ንጹሃን የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ አቅማቸው የፈቀደ ወደ ጫካ እየገቡ መሆናቸውን እና አቅመ ደካሞች እና ህጻናት ብቻ እንደቀሩ ነግረውናል፡፡

ትናንት ወደ ከተማዋ የገቡት የታጠቁ ኃይሎች በፓትሮል ተሸከርካሪዎች ከነፍስ ወከፍ መሳሪያ በተጨማሪ ሌሎች የቡድን መሳሪያዎችንም እንደያዙ ነግረውናል፡፡

ጥቃቱ በንጹሃን ወገኖች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነና መንግሥት አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጭዎቹ ጋር በነበረን የሥልክ ግንኙነት ወቅትም ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ድምጽ በአካባቢው መስማት ችለናል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጡን ለኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ደውለን ስልካቸው አልተነሳም፣ የሥራ ኀላፊዎችን ምላሽ እንዳገኘን ይዘን እንቀርባለን፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሙስና ላይ በተገኙ ግለሰቦች እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
Next articleባንኮች የግብርና ሥራን ለማዘመን የሚያግዙ ማሽኖችን መግዛት ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች የተሳለጠ ብድር ማቅረብ እንዳለባቸው ተመላከተ።