
አዲስ አበባ: ሕዳር 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የተደራጀ ሌብነት ከኑሮ ውድነትና ከሥራ አጥነት ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ለኢትዮጵያ ስጋት መኾኑ ተገልጿል።
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ሥራ መግባቱንና እርምጃ እየወሰደ መኾኑም ታውቋል።
በኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በተሰጠው መግለጫ ሙስናና ብልሹ አሠራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
በመንግሥት ተቋማት በልማት ድርጅቶችና በተለያዩ ተቋማት በተደረገው ጥናት ከኑሮ ውድነትና ከሥራ አጥነት በመቀጠል ለሀገሪቱ ስጋት መኾኑን ዳይሬክተር ጀኔራሉ ተናግረዋል።
የዚህ ኮሚቴ መቋቋም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሥራት ከቀበሌ እስከ ላይኛው እርከን የተንሰራፋውንና ሀገር እያጠፋ ያለውን ሙስና ለመቀነስ በትጋት ይሠራል ነው ያሉት።
ይህ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ እቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ የገባ ሲኾን እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ተናግረዋል።
የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዮስ በበኩላቸው በጥናቱ የተለዩትን የመንግሥት ግዥ፣ የጉምሩክ፣ የፋይናንስና ሌሎች ተቋማት ላይ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራና እርምጃዎች እየተወሰዱ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ አካባቢዎች መሬትን የመዘበሩ ደላላዎችና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መኾኑን ዶክተር ጌዲዮን ተናግረዋል።
የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የሠራቸውን ሥራዎች ለኅብረተሰቡ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሠራና ኅብረተሰቡም መረጃዎችን በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ተጠይቋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!