
ወልድያ: ሕዳር 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ መንግሥት በመደበው በጀት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የሀብት ማሰባሰብና የወደሙ መሰረታዊ አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በራያ ቆቦ ወረዳ ወርቄ ቀበሌ ተካሒዷል።
በመርኃ ግብሩ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደሱ እንደገለጹት በወረራው ወቅት የወገን ጦር ጋር በመናበብ አርበኝነቱንና ደጀንነቱን በተግባር አሳይቷል። በወረራው በተፈጸመብን ጥቃት ከ 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ውድመት ደርሶብናል ነው ያሉት።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈንታው ባታብል እንዳሉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት በዞኑ በፈጸመው ወረራ የጅምላ ጭፍጨፋና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።
ወረራውን ለመመከት መላ ሕዝቡ ከወገን ጦር ጋር በመሰለፍ የጠላትን ዓላማ አክሽፏል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው።
በተለይም የወርቄ ቀበሌ ሕዝብ አካባቢያቸውን ለጠላት ሳያስደፍሩ የአባቶቻችንን ጀግንነት ደግመዋል ብለዋል።
የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚያግዝ 110 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታሰቡንም ነው ያስታወቁት።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በወረራው ወቅት በራያ ቆቦ ወረዳ የወርቄ ቀበሌ ነዋሪዎች
የጽናት፣ የነጻነትና የአንድነት ተግባር መፈጸማቸውን አንስተዋል።
በመጀመሪያ ዙር ብቻ በተፈጸመብን ወረራ ከ292 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት እንደደረሰ በጥናት አረጋግጠናል ያሉት አቶ ስዩም ከዚያ በኋላ በተፈጸመብን ወረራ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2015 ዓ.ም ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ገልጸው የመልሶ ግንባታ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ከራሱ በጀት በመደበው 1 ቢሊዮን ብር ጉዳት በደረሰባቸው 8 ዞኖች የመልሶ ግንባታ ሥራው በቀጣይ ጊዜያት እንደሚካሔድ ያስታወቁት አቶ ስዩም የ3 ሺህ ቤቶች ግንባታ፣ 21 ትምህርት ቤቶች፣ የ10 ጤና ጣቢያዎችና የ1 ሆስፒታል፣ የ31 የንጹህ መጠጥ ውኃን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት የመልሶ ግንባታ ሥራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተገደን በገባንበት ጦርነት ነጻነትና ህልውናችንን ለማስጠበቅ መላው ሕዝባችን ከጸጥታ ኀይላችን ጋር በመሆን የፈጸሙት ጀግንነት በታሪክ የሚዘከር ነው ብለዋል።
የወርቄና አካባቢው ሕዝብ በወረራው ወቅት አኩሪ መስዋእትነት ከፍሏል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ አኩሪ ገድላቸውም ለክብርና ለህልውና መቀጠል የተከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ በመልሶ ግንባታ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ወቅት “የአማራና የትግራይ ሕዝብ መለያዬት የማይችል አንድ ሕዝብ ነው፤ የሚበልጥብን ሰላማችን ነው፤ የሚያጋጥም ችግር ቢኖር እንኳ በውይይት መፍታት እንጅ ወደ ጦርነት መግባት ያለፈበት አማራጭ ነው” ብለዋል።
ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት መደረጉን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ይህም ለሕዝብ እፎይታና ሰላም መስፈን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።
በጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለመገንባት መንግሥት በጀት መድቦ እየሠራ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ባለሀብቶችና ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:—ስማቸው እሸቴ–ከወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!