
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) ግብፅና ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት በንግግር ለመፍታት መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በሩሲያ ሶቹ ከተማ ተወያይተዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ከሩሲያ- አፍሪካው የጋራ የኢኮኖሚ ፎረም የጎንዮሽ መድረክ ላይ ዛሬ ረፋድ ባደረጉት ውይይት ግብፅ ወደ ቀድሞው የድርድር መድረክ እንደምትመለስ ፕሬዝዳንት ሲሲ እንዳረጋገጡላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡
የሀገራቱን ግንኙነት እያሻከረ ያለው የግብፅ ሚዲያዎች ዘገባ ስለመሆኑም ሁለቱ መሪዎች ተወያይተዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው የሦስቱ ሀገራት ቴክኒካል ኮሚቴ መድረክም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮችን ደግሞ በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት ከስምምነት መድረሳቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ሁለቱ አገራት የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነትና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን አጠናክሮ ለመስራትም ተስማምተዋል፡፡