
ባሕር ዳር: ሕዳር 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ2014 በጀት ዓመት እና የ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት አቅርቧል፡፡ የኮርፖሬሽኑን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ለምክር ቤት አባላቱ ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንተነህ መንግሥቴ የአማራ ሕዝብ የተከፈተበትን ወረራ እና ጦርነት በድል እንዲቀለበስ መረጃ በማቅረብ አይተኬ ሚናን ተወጥቷል ብለዋል፡፡
“አሚኮ ምቹ ባልኾኑ ሁኔታዎችም ለሕዝብ የሚሠሩ ባለሙያዎች፤ በጦርነት ውስጥ ገብተው ታሪክን ለትውልድ የሚያደርሱ ጋዜጠኞች ፈጥሯል” ያሉት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ክልሉ በገጠሙት የሕልውና ጦርነቶች ውስጥ በሚዲያው ዘርፍ ታሪክ የማይረሳቸውን ተግባራት አከናውኗል ብለዋል፡፡ በሕልውና ዘመቻዎቹ የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ከማርካት ባለፈ ሕዝብን በማነሳሳት እና በማጀገን በኩል አስተዋጽኦው የማይተካ ነበር ነው ያሉት፡፡
ኮርፖሬሽኑ የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍ፣ ማኅበረሰቡን በማንቃት እና ጦርነቱን የሚሸከም ክልላዊ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ጥረት አድርጓል ያሉት አቶ አንተነህ በክልሉ ውስጥ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ለሕዝብ መረጃን በማድረስም ግንባር ቀደም እንደነበር አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!