አሚኮ እያደገ የመጣውን የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ውድድር እና የሕዝብ ፍላጎት አጣጥሞ ለመሥራት በርካታ ለውጦችን እያደረገ ነው፡፡

108

ባሕር ዳር: ሕዳር 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔ በመጀመሪያው ቀን ውሎ ከሰዓት በኋላ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን የ2014 በጀት ዓመት እና የ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን እያዳመጠ ነው፡፡

የኮርፖሬሽኑን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤት አባላቱ ያቀረቡት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አንተነህ መንግሥቴ ተቋሙ እያደገ የመጣውን የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ውድድር እና የሕዝብ ፍላጎት አጣጥሞ ለመሥራት በርካታ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡

አሚኮ ለኅብረተሰብ ለውጥ በሚተጉ ሙያተኞች፣ ሥራ አስፈጻሚዎች እና የቦርድ አባላት የተዋቀረ ተቋም ነው ያሉት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው የኮርፖሬሽኑ የዕለት ከዕለት ተግባራትም ከተቋሙ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የተቀዱ ናቸው ብለዋል፡፡

አሚኮ ተግባራቱን ዳር ለማድረስም የይዘት፣ የቴክኖሎጂ እና የአስተዳደር የሙያ ስብጥር ያላቸው ሠራተኞችን ይዟል ያሉት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው የኮርፖሬሽኑን ራዕይ እና ተልዕኮ የሚያሳኩ ተቋማዊ እሴቶች አሉት ነው ያሉት፡፡ ሙያዊ መርህን ማክበር፣ ለሕዝብ በመወገን መሥራት፣ ጥበባዊ ፈጠራን በመጠቀም ተግባራትን ማከናወን እና በጋራ የመሥራት ባሕልን ማዳበር የተቋሙ እሴቶች መኾናቸውንም አቶ አንተነህ አንስተዋል፡፡

አሚኮ በ10 ቋንቋዎች፣ በአራት ጋዜጦች፣ በሰባት መካከለኛ ሞገድና የኤፍ ኤም ጣቢያዎች፣ በሁለት የቴሌቪዥን እና በበይነ መረብ አውታሮች የክልሉን እና የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ለሕዝብ ተደራሽ እያደረገ መኾኑን ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ አሚኮ በዋናነት ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን መረጃ በውጤታማነት ለማከናወን የሚያስችል የዜና ጉባዔ አለው ያሉት አቶ አንተነህ በ2014 በጀት ዓመት ከቀረቡት 1 ሺህ 857 ጥቆማዎች እና የይዘገብልን ጥያቄዎች መካከል ለሕዝብ የሚኖረው ፋይዳ እየተመዘነ ለ1 ሺህ 712 የዘገባ አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለውጥ የሚመጣው ለውጥን በመፈለግ ብቻ ሳይኾን ጠብታ ተግባርም ሲጨመርበት ነው” ዶክተር ማተብ ታፈረ
Next article“አሚኮ ምቹ ባልኾኑ ሁኔታዎችም ለሕዝብ የሚሠሩ ባለሙያዎች፤ በጦርነት ውስጥ ገብተው ታሪክን ለትውልድ የሚያደርሱ ጋዜጠኞች ፈጥሯል” የአሚኮ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንተነህ መንግሥቴ