
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የመንግስት አካላትና የፀጥታ ሀይሎች አካባቢውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆኑን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር አስታውቋል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአብመድ በሰጡት አስተያዬት ትናንት በርከት ያሉ ወጣቶች በዋና ዋና መንገዶች እየተዘዋወሩ በሰዎች ላይ ጥቃት፣ በንብረት ደግሞ ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ አለመረጋጋቱ እንደተከሰተም አስረድተዋል፡፡ የግጭቱ መንስኤ በአብዛኛዎቹ የኦሮሚያ ከተሞች ተስተውሎ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡
ዛሬ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00 ገደማ ጀምሮም አለመረጋጋቱ መቀጠሉንም አስታውቀዋል፡፡ እንደ ምንጮቻችን መረጃ በከተማዋ እለታዊ እንቅስቃሴ ተገትቷል፤ የንግድ ተቋማትም ተዘግተዋል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ተቋርጧል፡፡ በሁከቱ የተነሳ የሰዎች ህይዎት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ቤቶች መቃጠላቸውን እና ንብረትም መዘረፉን አስረድተዋል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ መረጃ የፀጥታ ሀይሎች በአካባቢው የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ ቢሆኑም ሙርቲ ጉቲ ተብሎ በሚጠራው አዲስ ሰፈር አለመረጋጋቱ ቀጥሏል፡፡
በተለምዶ ዝንጀሮ ገደል ተብሎ በሚጠራው የከተማዋ ክፍል ነዋሪ እናቶች ደግሞ አካባቢው ወደ ቀድሞው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ መንግስት ጥረት ማድረግ እንዳለበት ተማጽነዋል፡፡የፀጥታ አካላት ጥፋተኞችን ለህግ እንዲያቀርቡ እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ጠይቀዋል፡፡ ይህን በማድረግ ከተማዋን እንዲያረጋጉም ነው ነዋሪዎቹ የጠየቁት፡፡
አብመድ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እዝቂያስ ታፈሰን ስለ ጉዳዩ ጠይቋል፡፡ ከትናንት ምሽት ጀምሮ ሌሊቱን አንጻራዊ መረጋጋት የነበር ቢሆንም ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች አለመረጋጋት መከሰቱን አስረድተዋል፡፡
ትናንት በነበረው አለመረጋጋት የሰው ህይዎት ማለፉንም አስታውሰዋል፡፡ የከተማዋ የመንግስት አካላትና የፀጥታ ሀይሎች አካባቢውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ነው ኃላፊው የጠቆሙት፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ከፀጥታ ሀይሎች ጎን በመሆን ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንዲመለስ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ